ምክር ቤቶች የአስፈጻሚ አካላትን ተግባራት በመከታተል ፍትሐዊ የልማት ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ የካቲት 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤትና የብሔረሰቦች ምክር ቤት ከዞን ምክር ቤቶች ጋር 3ኛ ዙር የጋራ የምክክር ፎረም በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ላይ አካሂደዋል።
የፎረሙ ባለድርሻ አካላት በሸካ ዞን አንድራቻ ወረዳ ዮኪጭጭ ቀበሌ ተገኝተውየልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል፡
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ እንደ ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል በግብርናው ዘርፍ በእንሰት፥ በዓሳ እርባታ፣ በንብ እርባታ እና በቡና ምርት ላይ እየታየ ያለው መነቃቃት ሊበረታታ የሚገባው ነው ብለዋል።
የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኮ ምክር ቤቶች በአስፈጻሚ አካላት እንቅስቃሴ ላይ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ሁሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤትም የአፈጻጸም ፍትሐዊነትን እንደሚከታተል ተናግረዋል።
በዚህም ክልሉ ከተዋቀረ ወዲህ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ደረጃ በደረጃ እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ተናግረው ለአብነትም ይህ የምክክር ፎረም የተካሄደበት የሸካ ዞኑ ቴፒ ከተማ አሁን ላይ እየታየበት ያለው ሁለንተናዊ ለውጥ ማሳያ ነው ብለዋል።
የሸካ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ዮሐንስ ካሳሁን በበኩላቸው ከክልሉ የክላስተር ከተሞች አንዷ የሆነችው የቴፒ ከተማ ቀደም ሲል ከነበረችበት የጸጥታ ችግር በመላቀቅ መሰል ክልላዊ ፎረሞችን ማስተናገድ መቻሏ ሠላምና ጸጥታ የልማት ሁሉ መሠረት መሆኑን በመረዳት የክልሉ መንግሥትና ህዝብ በወሰዱት ቁርጠኛ አቋም የተነሳ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ስለልማት መነጋገርና የለማውን የዞኑን አካባቢ መጎብኘት በመቻላችን ደስታ ይሰማናል ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞናቸው፡፡
በዞኑ ውስጥ 46 ባለሀብቶች በግብርናው ዘርፍ ተሳትፈው እያለሙ የሚገኙ ሲሆን 85 ሺ ሄክታር ማሳ ቡና እንዲሁም 15 ሺ ሄክታር ማሳ ቅመማ ቅመም ምርት በባለሃብቶቹ እየለማ ነው ብለዋል፡፡
የተገኘውን ሠላም አጠናክሮ ለማስቀጠል የክልሉ መንግሥት ክትትልና ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በሸካ ዞን አንድራቻ ወረዳ የዮኪጭጭ ቀበሌ ሞዴል አርሶ አደሮች የእንሰት ምርት፥የማር ምርት፥ የዓሳ እርባታ እና በአካባቢው የሚገኘው የጸጋ ውሃ ፋብሪካ የመስክ ምልከታው አካል ነበሩ።
ዘጋቢ፡ አስታወሰኝ በቃሉ – ከማሻ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ