በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ሀዋሳ፡ የካቲት 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) አጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጲያ የተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለሚገኙ 50 አካል ጉዳተኞች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ በክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ  ቢሮ አማካኝነት ከአጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጵያ ግብረ ሠናይ ድርጅት የተገኘ መሆኑን የቢሮው ሃላፊ ወይዘሪት ቤተልሄም ዳንኤል ገልጸዋል።

በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ኋላቀር አመለካከቶችና ምቹ ያልሆኑ አካባቢዎች ያልተፈቱ የአካል ጉዳተኞች ችግሮች ናቸው ያሉት ወይዘሪት ቤተልሄም አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ዜጋ ክብራቸው እና  መብቶቻቸው ሊጠበቅ  እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ቢሮው በክልሉ ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች የተለያዩ ድጋፍና እርዳታ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን አስታውሰው ለ50 አካል ጉዳተኞች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የአካል ድጋፍ መሳሪያዎች የዊልቸር ድጋፍ መደረጉን  ገልጸዋል።

በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳዳር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓልማው ዘውዴ በበኩላቸው በከባድና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ችግርን ለማቃለል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

አጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጲያ የተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ላደረገው የዊልቸር ድጋፍ ምሥጋና አቅርበው መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የአጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጵያ አስተባባሪ ሲስተር ሳባ ተክለ ማርቆስ ድርጅቱ የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሕፃናትንና በተለያዩ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ የተለያዩ የአካል ድጋፎች ላይ ድርጅታቸው እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው  የተጀመረው ድጋፍ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡

ድጋፍ የተደረገላቸው አካል ጉዳተኞችም ከዚህ ቀደም የዊልቸር ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ገልጸው በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውንና ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል፡፡

በድጋፍ ርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ ከክልል እና ከዞን የተወጣጡ አመራሮች እንዲሁም ድጋፍ የተደረገላቸው አካል ጉዳተኞች ተገኝተዋል፡፡

 ዘጋቢ፡ በየነ ወርቁ – ከሚዛን ጣቢያችን