የሀገሪቱን ቱሪዝም ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶች በሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰሩ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል – አቶ አንተነህ ፍቃዱ

የሀገሪቱን ቱሪዝም ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶች በሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰሩ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል – አቶ አንተነህ ፍቃዱ

ሀዋሳ፡ የካቲት 16/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀገሪቱን ቱሪዝም ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶች በሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰሩ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፍቃዱ ገለፁ።

በክልሉ ሆሳዕና ከተማ በ1 መቶ 75 ሚሊየን ብር ካፒታል የተገነባው ባለ 3 ኮከብ ገብረጻድቅ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በ2040 ኢትዮጵያን በአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ከታቀዱ አምስት የልማት ምሰሶዎች የኢንዱስትሪ ዘርፍ አንዱና ግንባር ቀደም መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማሳደግ ከፍተኛ ድርሻ ያለውን የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ ባለሀብቶች እያደረጉ ያለው ጠንካራ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የሀገር ብልጽግና የሚያረጋግጠውንና የተለያዩ ሀገራዊና አለምአቀፋዊ መድረኮችን ለማስተናገድ ወሳኝ የሆነውን ሆቴልና ቱሪዝምን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አቶ አንተነህ ገልፀዋል።

ጂቲ ዳራጎ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አካል የሆነው ባለ 3 ኮከብ ገብረጻድቅ ኢንተርናሽናል ሆቴል በ175 ሚሊየን ብር ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን የገለጹት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ገብረጻዲቅ ናቸው።

ማህበሩ በአካባቢው በ2 ሚሊየን ብር አንድ ትምህርት ቤት ገንብቶ መስጠቱን የጠቆሙት አቶ ደሳለኝ በኮንስትራክሽን፣ በሆቴልና ቱሪዝምና በነዳጅ ማዳያ ዘርፎች በመሰማራት ከፍተኛ ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል።

ማህበሩ ከ3 መቶ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን የገለጹት አቶ ደሳለኝ በዕለቱ የተመረቀው ሆቴልም ለ200 ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሊሩ ጀማል ከተማው ከ3 ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸው በተላይም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የመጣው ለውጥ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ከተማን ማሳደግ የሁሉንም አካላት ትብብርና ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ የተጀመረው የህብረተሰብ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የሆቴልና ቱሪዝም መስፋፋት ለከተማ ዕድገትና ለገቢ ምንጭ ወሳኝ ከመሆኑም ባሻገር የስራአጥነት ችግርን የሚቀርፍ መሆኑንም በመጠቆም።

የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ በበኩላቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ዕድገት የሚውሉ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት በመሆኗ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ግብ ከተጣለባቸው ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም መሆኑን ተናግረዋል።

ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ወሳኝ የሆነውን ሆቴልና ቱሪዝምን ማሳደግ እንደሚገባ የገለፁት አቶ አብርሃም ዘርፉ የስራአጥነት ችግርን ለመቅረፍና የገቢ አቅምን ለማሳደግ አጋዥ መሆኑን አመላክተዋል።

ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በከተማው ከ1.5 ቢሊየን በሚበልጥ በጀት ደረጃቸውን የጠበቁ የአስፋልትና የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ስራ እየተሰራ ሲሆን ዘላቂ የውሃ፣ የመብራትና ቴሌኮም የማሟላት ስራም በትኩረት እየተሰራ በመሆኑ ባለሀብቶች ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው በኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት አለባቸው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በዕለቱ የተመረቀው ገብረጻድቅ ኢንተርናሽናል ሆቴል ቤተሰቦችና ሌሎች ባለሀብቶቹ ከዚህ ቀደም በራሳቸው ጥረት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተሰማርተው ላሳዩት ለውጥ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ አብርሃም በቀጣይም ዘርፉን ለማሳደግ በመንግሥት መዋቅር አሰራር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመቅረፍ ቀልጣፋ አገልግሎትና ድጋፍ ለመስጠት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ዘጋቢ: ሳሙኤል መንታሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን