የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር የተጀመሩ የሰላም፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን የበለጠ ስኬታማ ለማድረግ ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ከተማ አስተዳደሩ ጥሪ አቀረበ
ሀዋሳ፡ የካቲት 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በከተማው የተጀመሩ የሰላም፣ የልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም ሌሎች ተግባራትን ይበልጥ በማጠናከር ከተማዋ ውብ፣ ምቹና ለኑሮ ተስማሚ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን በየደረጃው ለሚደረገው እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ ያለውን ድጋፍና ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ እንዲቀጥል ከተማ አስተዳደሩ ጥረ አቅርቧል።
ከተማዋ በ9ኛው ሀገር አቀፍ የከተሞች ፎረም ውድድር ከምድብ 2 ከተሞች 1ኛ በመውጣትዋ
የከተማው ከንቲባ አቶ አብዶ አህመድ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዶ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት ቡታጅራ ከተማ ዘንድሮ በወላይታ ሶዶ ከተማ በተካሄደው በ9ኛው የከተሞች ፎረም ውድድር ላይ በምድብ 2 ከተሞች 1ኛ በመውጣት አሸናፊ በመሆኗ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
መንግሥት ከለውጡ ዓመታት ወዲህ በሀገር ደረጃ ለከተሞች ልዩ ትኩረት በመሥጠት የከተሞችን ልማት በማፋጠን ተወዳዳሪ አንዲሆኑ ጭምር በማሰብ ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎችን አዘጋጅቶ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እየሰራ በመሆኑ በየደረጃው ለውጥ እየተመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የሚገኙ 124 ከተሞችን ያሳተፈው የዘንድሮው 9ኛው የከተሞች ፎረም ከሌሎች ሁነቶች በተጓዳኝ የከተሞች ራስን የማስተዋወቅ ውድድር መከናወኑን ጠቁመው ተሳታፊ ከተሞቹ በየደረጃቸው በ4 ምድቦች ተከፍለው በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ለየምድቡ በቀረቡ የመወዳደሪያ መስፈርቶች መመዘናቸውንና በዚህም ከየምድቡ ከ1ኛ እስከ 3ኛ የወጡ ከተሞች መለየታቸውን ተከትሎ ከምድብ ሁለት ቡታጅራ ከተማ 1ኛ በመውጣት አሸናፊ መሆኗን አስረድተዋል።
ከተማዋ በፎረሙ ያስመዘገበችው የላቀ ውጤት የመላው የከተማው ማህበረሰብ፣ የአመራሩ፣ የባለሙያውና በየደረጃቸው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት ውጤት እና የመትጋት ፍሬ መሆኑን በመግለጽ ለዚህም ውጤታማነትም ያላሰለሰ ጥረት ላደረጉ አካላት ከተማ አስተዳደሩ ከፍ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል ብለዋል።
የቡታጅራ ከተማ የከተማ አስተዳደርነት ዕውቅና ካገኘች ገና 20 ዓመታትን ያስቆጠረችና ከዕድሜዋ በላይ አበረታች ዕድገት ላይ የምትገኝ ሲሆን ዕድገቷ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ያሏትን አቅም፣ ፀጋዎችና ዕድሎችን በማስተሳሰር የተሻለች፣ ተወዳዳሪና ስማርት ከተማ እንድትሆን በትኩረት መሥራትን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
በከተማዋ በተለይም አሁን ላይ ህዝቡንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በርካታ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛል ያሉት ከንቲባው፥ በከተማው የተጀመሩ የሰላም፣ የልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም ሌሎች ተግባራትን ይበልጥ በማጠናከር በቀጣይ ከተማዋን ውብ፣ ምቹና ለኑሮ ተስማሚ፣ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን በየደረጃው በሚደረገው እንቅስቃሴ መላው የከተማው ማህበረሰብ፣ አመራሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በየደረጃው እያደረጉት ያለውን ድጋፍና ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አበክረው ጠይቀዋል።
በተለይም በኢንቨስትመንት ዘርፍ በከተማዋ ለሚሰማሩ አልሚ ባለሀብቶች በሁሉም ዘርፎች ምቹ ሁኔታዎች በመኖራቸው ሁሌም በራችን ክፍት በመሆኑ ወደ ሰላም፣ ልማትና አንድነት ሰገነት ወደሆነችው ከተማዋ በመምጣት እንዲያለሙ ከንቲባው አቶ አብዶ አህመድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሑር – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ