ሰዎችን በማስገደድና በማጭበርበር የገንዘብ ዝውውር በማድረግ ጉዳት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ህገ ወጦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ
ሀዋሳ፡ የካቲት 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሰዎችን በማስገደድ እና በማጭበርበር የገንዘብ ዝውውር በማድረግ ጉዳት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ህገ ወጦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
በተለይም ባለሀብቶች እና የባንክ ሰራተኞች ላይ ያነጣጠረ ውንብድና እንዲሁም አጠራጣሪ ነገር ሲገኝ ለፀጥታ አካላት መጠቆም እንደሚገባም ተመላክቷል።
የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ እንስፔክተር ደበበ ኦንቶ እንደገለፁት የባንክ ማናጀሮችን በማስፈራራት እና በመደለል ከፍተኛ ገንዘብ ዝውውር ለማድረግ ሲሞክሩ የነበሩ 4 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ አካባቢም ሶስት ግለሰቦችን በማፈን አንዱ ኢትዮ ኮንስትራክሽን ሆሳዕና ቅርንጫፍ 151 ሚሊየን ብር እና አሁለት ግለሰቦች 68 እና 13 ሚሊየን ብር ዝውውር ያደረጉ ሲሆን በአርባምንጭ ከተማ ዳሽን ባንክ ሰራተኞችንና ስራ አስኪያጁን ለማሳሳት ሲሞክሩ በደረሰ ጥቆማ መያዛቸውን ገልፀዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በመረጃ ደህንነት እና በሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች የጋራ ጥረት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የገለፁት ኢንስፔክተር ደበበ በርከት ያለ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ሰዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የፀጥታ አካል በመምሰል ለጥያቄ ተፈልገዋል እያሉ ግለሰቦችን ይዘው የሚሰወሩ እና ገንዘባቸውንም የሚያዛውሩ መሆኑን ህብረተሰቡ በመረዳት እንደዚህ አይነት አጠራጣሪ ነገር ሲገኝ ወዲያው ለፀጥታ አካላት ማሳወቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡ ገነት መኮንን – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ