ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የህዝብና የመንግስት አገልግሎቶችን የሚያፋጥን በመሆኑ ለሁሉም ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የህዝብና የመንግስት አገልግሎቶችን የሚያፋጥን በመሆኑ ለሁሉም ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 09/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የህዝብና የመንግስት አገልግሎቶችን የሚያፋጥን በመሆኑ ለሁሉም ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በከምባታ ዞን የቃዲዳ ጋሜላ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።

ያነጋገርናቸው አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎችም ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት አገልግሎቱን ለማግኘት እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ባለፉት አመታት ተግባራዊ የተደረገዉ የፋይዳ ብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ለሀገራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መሠረት እየጣለ እንደሆነና የዜጎችን ማህበራዊ አገልግሎቶት የመጠቀም ዕድል እያቀላጠፈ እንደሚገኝ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት መረጃዎች ያመላክታሉ።

ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ በአገልግሎት ሰጭና ተቀባይ መካከል መተማመን እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር፥ የባንክ አገልግሎቶችን በማፋጠን የማጭበርበር ወንጀሎች እንዲቀንሱ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለፁት በከምባታ ዞን የቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ማርሻዬ ከበደ ናቸው።

ዘርፉ በፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ እንደሚመራ ጠቁመው፥ ወረዳው በሁሉም አከባቢዎች ካርዱን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።

ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ለማግኘት ዜጎች በአቅራቢያቸው ከሚገኙ ባንኮች፣ ከኢትዮ ቴሌኮምና ከፖስታ ቤት በአካል በመሄድና ማንነትን የሚገልፁ ማስረጃዎችን በማቅረብ እንዲመዘገቡ የግንዛቤ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በ2018 ዓ ም በወረዳው በአጠቃለይ 52 ሺ በላይ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ተቅዶ 35 ሺ በላይ ለማድረስ እንደተቻለና አሁንም ስራው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ዲጂታል መታወቂያ የሰው ልጅ በየትኛውም የሀገሪቱ አከባቢ እራሱን ሆኖ እንዲኖር የሚያደርግ ፥በሁሉ ዐቀፍ የሀገሪቱ አገልግሎት እኩል እንዲሳተፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።

ማህበራዊ አገልግሎቶች ያለዲጂታል መታወቂያ የሚገደቡ መሆናቸውን በመገንዘብ ዜጎች በወቅቱ ተመዝግበው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ወ/ሮ ማርሻዬ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የህዝብና የመንግስት አገልግሎቶችን የሚያፋጥን መሆኑን በመገንዘብ እየተጠቀሙ መሆናቸውን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል ።

ዘጋቢ: አለማየሁ ማተቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን