አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል እንግሊዝ ወደ ፍፃሜ ባለማለፏ ከፍተኛ ትችትን አስተናገዱ
በአትላንታ በተደረገው የዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ እንግሊዝ በአርጀንቲና 2 ለ 1 ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ ከሆነች በኋላ፣ የቡድኑ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል በወሰዷቸው የመከላከል ውሳኔዎች ምክንያት ከታዋቂ ተንታኞች እና ጋዜጠኞች በኩል ከፍተኛ ትችትን አስተናግደዋል።
እንግሊዝ ቀድማ መሪ መሆን ብትችልም፣ ቱኸል በጨዋታው 71ኛ ደቂቃ ላይ ሶስት ተከላካዮችን እና አደረጃጀታቸውን ወደ አምስት ተከላካይ በመቀየር ቡድኑ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ማድረጋቸው የሽንፈቱ ዋና ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል።
ቡድኑ ይህንን ታክቲክ ከተከተለ በኋላ ላለፉት 21 ደቂቃዎች 93 በመቶ ያህሉን ኳስ ለአርጀንቲና አሳልፎ የሰጠ ሲሆን፣ ግብ ካገባ በኋላም በአርጀንቲና የግብ ክልል ውስጥ አንድም ኳስ መንካት አልቻለም።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የእግርኳስ ተንታኞች እና የቀድሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች አሰልጣኙን ተችተዋል።
ከተችዎች መካከል አንዱ የሆነው የቀድሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ዌይን ሩኒ እንደተነገረው “የቶማስ ቱኸል ውሳኔዎች እንግሊዝን ዋጋ አስከፍለዋታል” ብሏል።
ሌላኛው የቀድሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አላን ሺረር በሰጠው አስተያየት “እንደ ኖርዌይ እና ሜክሲኮ ያሉ ቡድኖችን ወደ ኋላ አፈግፍገህ ልታሸንፍ ትችላለህ፣ አርጀንቲና ግን ባላጋራን የመቅጣት ከፍተኛ ብቃት እና የኳስ ቁጥጥር ያላት በመሆኑ አሸንፋለች” ሲል ተናግሯል።
ማይክል ኦዌን በበኩሉ “ስፔን 1 ለ 0 ስትመራ ያሳየችውን ድፍረት እና የላቀ የማሸነፍ መንፈስ ተመልከቱ፤ ከዚያ ደግሞ እንግሊዝን ተመልከቱ። እኛ ከአርጀንቲና የተሻልን ቡድን ነበርን ነገር ግን መሸነፍ ይገባን ነበር። 1 ለ 0 እየመሩ ሶስት ተከላካዮችን መቀየር ለተጫዋቾች ምን ዓይነት መልእክት ያስተላልፋል?” በማለት ቁጭቱን ገልጿል።
የቀድሞ የጀርመን እና ባየርን ሙኒክ አጥቂ ቶማስ ሙለር በሰጠው አስተያየት “እንግሊዝ መሪ ከሆነች በኋላ ጨዋታውን የያዘችበት መንገድ ጨርሶ ሊገባኝ አልቻለም። አርጀንቲናዎች ምቹ ቦታ ላይ ሆነው ተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ ግብ ክልል እንዲያሻግሩ እንዴት መንገድ እንደሚከፈትላቸው አይገባኝም” ሲል ተደምጧል።
ጋሪ ኔቪል ደግሞ እንግሊዝ ወደ ፍፃሜ ለማለፍ ከዚህ የተሻለ እድል እንደማታገኝ ገልጾ፣ ቡድኑ በጣም ወደ ኋላ ማፈግፈጉ የቡድኑን የማሸነፍ ተነሳሽነት እና የአዕምሮ ጥንካሬ ክፍተት እንደሚያሳይ ተናግሯል።
ፖል ሜርሰን በበኩላቸው ጋሬዝ ሳውዝጌት በመከላከሉ ሲተቹ እንደነበር አስታውሰው፣ ቱኸል ግን የተለየ አቀራረብ ይዞ ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ ተመሳሳይ ስህተት መስራቱን ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ አስፈረመ
ማንቸስተር ዩናይትድ አንድሬ ሳንቶስን አስፈረመ
የ2018 የCBE የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን በማሸነፍ ሁለት ዋንጫ ላነሳው የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ክልሉ ያዘጋጀውን የዕውቅናና የሽልማት ፕሮግራም ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 06/2018 ከቀኑ 12፡00 ጀምሮ በሀዋሳ ሀይሌ ሪዞርት ይካሄዳል።