የጠምባሮ ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች የመኸር እርሻ የማሳ ዝግጅት ቢያደርጉም በቂ ግብዓት አለማግኘታቸውን ገለጹ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 09/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጠምባሮ ልዩ ወረዳ በ2018/19 የመኸር እርሻ የማሳ ዝግጅት ሥራ ቢያከናውኑም በቂ ግብዓት እያገኙ ያለመሆናቸውን የጠምባሮ ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
በወረዳው እያጋጠመ ያለውን የግብዓት እጥረት ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የልዩ ወረዳው ግብርና ጽ/ቤት አስታውቋል።
በልዩ ወረዳው ያነጋገርናቸው አንዳንድ አርሶ እደሮች ለመኸር እርሻ ተገቢውን የማሳ ዝግጅት ሥራ ቢያከናውኑም የግብዓት አቅርቦት በቂ ያለመሆኑን ገልጸው፥ ዘንድሮ ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት በበልግ እርሻ ሥራ ወቅት በምርት ከተሸፈነው ማሳ መካከል አብዛኛው የበቆሎ፣ የቦሎቄ እና የጎደሬ ማሳዎች ላይ ያለው ምርት በመበላሸቱ ለመኸር እርሻ መልሰው እያለሙ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ በእጃቸው ያለው የግብዓት መጠን ካዘጋጁት ማሳ ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ ባለድርሻ አካላት መፍትሔ እንዲያበጁላቸው ጠይቀዋል።
በልዩ ወረዳው የባችራ ቀበሌ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ታምራት ለፌቦ እና የቀበሌው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታድዮስ ብርሃኑ፥ በቀበሌው በበልግ እርሻ ወቅት ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት የተበላሸውን ማሳ ጨምሮ 722 ሄክታር መሬት ለመኸር እርሻ ሥራ ተገቢው የማሳ ዝግጅት ሥራ ተጠናቆ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።
የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መብራቱ አበራ እንደ ልዩ ወረዳው በበልግ እርሻ ሥራ ወቅት ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ሳቢያ የአዝርዕትና ሆልቲካልቸር ማሳ በመበላሸቱ በዘንድሮ የመኸር እርሻ 12 ሺህ 500 ሄክታር ማሳ እንደገና በማልማት በዘር ለመሸፈን እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።
አሁን እየቀረበ ያለው ግብዓት በቂ ባለመሆኑ እንደየአከባቢው የአየር ሁኔታ ቀድሞ ለሚያስፈልጋቸው ቅድሚያ በመስጠት የማዳረስና ለሌሎችም ግብዓት ተደራሽ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል ።
የልዩ ወረዳው ህብረት ሥራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ማቴዎስ በበኩላቸው ቀድሞ የደረሰው ግብዓት ስርጭት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፥ ለልዩ ወረዳው ለማቅረብ ከተያዘው 14ሺ ኩንታል ማዳበሪያና ዩሪያ አሁን ላይ 2 ሺህ 200 ኩንታል ማዳበሪያና 3ሺህ 600 ኩንታል ብቻ ዩሪያ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል ።
የአቅርቦት እጥረት ችግሮችን ለመፍታት ከክልሉ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑን አቶ ሙልጌታ ገልፀዋል።
ዘጋቢ : ሙሉነሽ ለማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2019 ጠቋሚ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው
ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የህዝብና የመንግስት አገልግሎቶችን የሚያፋጥን በመሆኑ ለሁሉም ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በርስ ግንኙነትና አንድነትን የሚያጠናክር ተግባር መሆኑ ተገለጸ