የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2019 ጠቋሚ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው

የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2019 ጠቋሚ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 09/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2019 ጠቋሚ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሳውላ ከተማ እየመከረ ነው፡፡

የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አጉኔ አሾሌ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ የሚከሰቱ የህብረተሰብ የጤና ስጋቶችን ለመቆጣጠር ኢንስቲትዩቱ መዳረሻውን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በበጀት ዓመቱ ማተኮሩን ገልፀዋል፡፡

በጤና ስጋቶች ላይ ምርምርና ቅኝት በማድረግ፣ ብሎም ሳይንሳዊ መረጃዎችን በማመንጨት ለስልታዊ እቅዶችና ተግባራትን እውን መሆን ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ሥርዓቱንና የጤና ደህንነትን የማጠናከር ስራ በስፋት መሰራቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ሥርዓቱንና የጤና ደህንነትን የማጠናከር ስራ በስፋት መሰራቱንም አስረድተዋል፡፡

የጤና ጉዳይ ድንበር የለሽ በመሆኑ ተቀራርቦ መስራትን እንደሚጠይቅ አንስተው፥ ኢንስቲትዩቱን ችግር ፈቺ እና ውጤታማ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ (ኢ/ር) በበኩላቸው የጤናው ዘርፍ ለሁለንተናዊ ብልፅግና ያለውን ሚና ለማጎልበት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለተሻለ የማህበረሰብ ጤና ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

ጥራት ያለው የላብራቶሪ ምርመራ ውጤት ለህሙማን ደህንነትና ለተሻለ ጤናማ ዜጋ የሚኖረው አበርክቶ የላቀ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በመድረኩ የክልሉ የጤና ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮችና ከሁሉም መዋቅሮች የተገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን