የመጠጥ ዉሃ ባለመኖሩ በስራቸዉ ላይ ችግር እየፈጠረባቸዉ መሆኑን በስልጤ ዞን ሁልባረግ ወረዳ ሀጂ ካሚልና ቤተሰቡ በወተት ላሞች እርባታ የተሰማሩት የግል ባለሀብት ሀጂ ካሚል ሰማን ተናገሩ

የመጠጥ ዉሃ ባለመኖሩ በስራቸዉ ላይ ችግር እየፈጠረባቸዉ መሆኑን በስልጤ ዞን ሁልባረግ ወረዳ ሀጂ ካሚልና ቤተሰቡ በወተት ላሞች እርባታ የተሰማሩት የግል ባለሀብት ሀጂ ካሚል ሰማን ተናገሩ

የሁልባራግ ወረዳ አስተዳደር በበኩሉ የዉሃ አቅርቦት ችግርን በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ሀጂ ካሚል ሰማን በሁልባራግ ወረዳ ባለፈዉ ዓመት ሀምሳ የተሻሻለ ዝሪያ ያላቸዉ ላሞችን በዘጠኝ ሚሊዮን ብር ገዝተው በማቅረብ ለወረዳና ለዞኑ ማህበረሰብ የወተት ፍላጎትን ለማሟላት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እያሉ የመጠጥ ዉሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ስራቸዉን ለማስቀጠል አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ የወተት ላሞች ሁኔታዉ ተመቻችቶላቸው ወደ ማዕከሉ ቢገቡ በአማካይ በቀን ሁለት ሺ ሊትር ወተት ለአካባቢዉ ህብረተሰብ ማቅረብ የሚችሉበት አቅም እንዳላቸዉም ባለሀብቱ ገልፀዋል።

በቅድመ ዝግጅት ወቅት ለላሞቹ የሚያስፈልገዉን ማደሪያና መኖ የማቅረቡን ስራ በመስራት እየተስተዋለ ያለዉ የዉሃ ችግር በዘላቂነት እንዲፈታላቸው ለሚመለከተዉ አካል በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን ተገቢዉን ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውን ጠቁመዋል።

ሀጂ ካሚል የዉሃ አቅርቦት ችግሩን በግላቸው ለመቅረፍ ቢሞክሩም ከአቅማቸዉ በላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሁልባራግ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽፋ አምዳለ በአሁኑ ወቅት ባለሀብቱ ያጋጠማቸውን የዉሃ አቅርቦት ችግር በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

ባለሀብቱ በወረዳዉ በወተት ላሞች እርባታ ስራ ተሰማርተዉ መስራታቸዉ ለህብረተሰቡ የወተት ፍላጎትን ከማሟለት አንፃር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎለ በመሆኑ አስፈላጊዉን ሁሉ እገዛ እንደሚያደርጉ ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል::

ዘጋቢ፡ ሀጀራ ግርማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን