የመግባቢያ ስምምነቱን የጂንካ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ምርመራ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ አለሙና በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የጂንካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉዋስ አቲሳ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱ በሁለቱም ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር በቀጠናው የሚሰሩ የልማት ሥራዎችን በሚዲያው ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው።
የጂንካ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ምርመራ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ አለሙ ከደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋር ዩኒቨርስቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሚዲያው ዘርፍ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመው የአሁኑ መግባቢያ ስምምነት ህጋዊ በሆነ መንገድ ዩኒቨርስቲው የሚያከናውናቸውን ሁሉ አቀፍ ልማት፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን በሚዲያው ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑና ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር የሚያስችል ስምምነት ነው ብለዋል።
በደቡብ ሬዲዮና ቴለቪዥን ድርጅት የጂንካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉዋስ አቲሳ የመግባቢያ ስምምነቱ ሚዲያው በቴክኖሎጂ ዘመኑ የደረሰበትን ደረጀ እንዲደርስ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመሰጠት ለቀጠናው የሚዲያ ተደራሽነት ጠንካራ እንዲሆን ለማድረግ ከዩኒቨርስቲው ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ተቋሙን የሚደግፍ ነው ብለዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም የጂንካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በአሁኑ ወቅት የሦስት ዞኖች ማለትም የኣሪ፣ የደቡብ ኦሞና የኧሌ ዞኖችን የሚዲያ ሥራዎችን በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በማህበራዊ ሚዲያ እየሸፈነ መሆኑን ጠቁመው በ13 ቋንቋዎች የሬድዮ ስርጭት እያደረገ መሆኑን ተናገረዋል።
ተቋማቸውም በቀጣይ ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተለያዩ ትብብር ዘርፎች ጥሩ ግንኙነት እንዲኖርና በሚዲያው ዘርፍ በልዩ ሁኔታ ለመስራት መታቀዱን አብራርተዋል።
በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ የተገኙት የጂንካ ዩኒቨርስቲ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያና የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህር ሄሬዲን መሐመድ ሁለቱም ተቋማት ለማህበረሰቡ ከሚሰጡት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት በተሻለ ሁኔታ ለመሰራት የመግባቢያ ስምምነቱ ውሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመው በዩኒቨርስቲው የሚከናወኑ የመማር ማስተማርን ተግባርን ጨምሮ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሥራዎችን በሚዲያው ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነቱ ፋይዳው ከፈተኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይም በደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የጂንካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የማኔጅመንት አባላትና የጂንካ ዩኒቨርስቲ ትስስርና የቴክኖሎጂ ደይሬክተርና ሌሎች የሚዲያው ዘርፍ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ