በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ሁሉም የበኩሉን እገዛ ማበርከት ይገባዋል – አቶ አልማው ዘውዴ
ሀዋሳ፡ የካቲት 08/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ሁሉም የበኩሉን እገዛ ማበርከት ይገባዋል ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ገልፀዋል፡፡
በታርጫ ከተማ የህዝብ ውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
“ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በታርጫ ከተማ በተካሄደው የህዝብ ውይይት ከተለያዩ ማህበራዊ መሠረቶች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሣትፈዋል።
የለውጡ መንግስት በውይይት ያምናል ያሉት የታርጫ ከተማ ከንቲባ ዳዊት ወንድሙ ከለውጥ ጊዜ በኋላ የታርጫ ከተማ የክልል ክላስተር ከተማ በመሆን ፈጣን እድገትም እያሳየች ትገኛለች ብለዋል።
የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ከተማ አስተዳደሩ ነዋሪ ህዝብን በማሳተፍ በርብርብ እየሰራ ይገኛል ያሉ ሲሆን በህዝብ ዘንድ ቅሬታ ሲፈጥሩ የቆዩ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ውይይት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የዳውሮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳደር አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው የ23 ዓመት ዕድሜ ያላት የታርጫ ከተማ ከለውጡ መንግስት በኋላ ፈጣን ዕድገት እያሳየች ያለችና ሠላም የሠፈነባት ከተማ ናት ብለዋል።
የታርጫ መጠጥ ውሃ ግንባታ፣ የከሰል ድንጋይ ማበልፀጊያ ፋብሪካ ግንባታ እና መሰል ለውጦች ለከተማው ዕድገት ከፍተኛ እገዛ የሚያበረክት መሆኑንም በአብነት ጠቅሰዋል።
የተጀመረው የአስፋልት መንገድ ግን የካሳ ክፍያ ያለመከፈል፣ የታርጫ ካምፓስ ግንባታ መስተጓጐል፣ የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራን ከማሳደግ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች መፈታት ያለባቸው መሆናቸውንም አንስተዋል።
በውይይቱ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፤ መንግስት የሀገራችን የለውጥ ጉዞ ውስጥ የህዝብን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በርካታ ተግባራትን መፈፀም ችሏል ብለዋል።
በከተሞች በአካቢያዊ፣ ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ያለመ የውይይት መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሀገራችን የለውጥ ጉዞ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ችግሮች የተከሰቱ ቢሆንም ይህን በመቋቋም ለውጡን በማስቀጠል እምርታዊ ለውጥ እየተመዘገበ ቢሆንም አሁንም ዘላቂ ሠላምን በማስጠበቅ ያለንን ሀብት እንዴት ተጠቅመን የብልፅግና ጉዞን ማስቀጠል አለብን በሚሉ ጉዳዮች ላይ መወያየት ማስፈለጉን አንስተዋል።
በውይይቱ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፣ የዳውሮ ዞን ምክትል ዋና ዳዊት ገበየሁ፣ የከተማ አስተዳደሩ ካንቲባ አቶ ዳዊት ወንድሙ እና ሌሎች የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የመንግስት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ