ባለፉት አመታት ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ዕውቅና ያገኘ ሁለንተናዊ ለውጥ አምጥታለች -አቶ አንተነህ ፍቃዱ
ሀዋሳ፡ የካቲት 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፉት አመታት ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ዕውቅና ያገኘ ሁለንተናዊ ለውጥ አምጥታለች ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ተናገሩ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በማህበራዊ ክላስተር ሥር የሚገኙ ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ የመንግስት ሰራተኞች” ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ቃል ስልጠና ወስደዋል ።
ስልጠናው የመንግስት ሰራተኛው በመንግሥት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ላይ እንዲሁም በሀገሪቱ ወቅታዊ ልማታዊ እንቅስቃሴ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያሰበ ነው።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እንዲሁም የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በዚህ ወቅት እንደገለፁት ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ለአለም ሀገራት ምሳሌ የሚሆን የኢኮኖሚ እምርታ እያሳየች መቆየቷን ያነሳሉ።
ከአስራ አምስት አመታት በላይ ኢኮኖሚዋን ከሁለት ዲጂት በላይ አሳድጋለች። ይሄን ማድረግ የቻሉት ደግሞ ጥቂት ሀገራት ብቻ ናቸው ብለዋል።
አቶ አንተነህ እንዳብራሩት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ላይ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ መሆኑን በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ ስድስተኛ ላይ መቀመጡ የኢኮኖሚውን ጥንካሬ አመልካች ነው ።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አምና 7 ነጥብ 5 በመቶ ዘንድሮ ደግሞ 7 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል።
የአለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ትንበያ ጋርም የተቀራረበ ውጤት መሆኑንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል ።
ይህ ሁሉ አመርቂ ውጤት በሀገራችን ስመዘገብ እጅግ በርካታ ችግሮች ተፈታትነውናል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተደጋጋሚ ድርቅ፣ የሰሜኑ ጦርነት፣ የፀጥታ ችግር ፣ የተለያየ ሀገራት ጫና ፣ አለም አቀፋዊ እና ወቅታዊ የፖለተካ ምህዳር፣ የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደራቸውን አንስተዋል ።
ጫናዎችን በመሻገርም አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት እጅግ የበለፀገች ሀገር ናት፦ ይሄን ሀብት ደግሞ ወደ ብልፅግና መቀየር የትውልዱ ሀላፊነት ስለመሆኑም ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፍቃዱ አሳስበዋል ።
ዘጋቢ : ጀማል የሱፍ
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ