በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ የዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በወረዳው በሰሜን በሌሳ ቀበሌ በይፋ ተጀመረ
ሀዋሳ፡ የካቲት 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ የዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በወረዳው በሰሜን በሌሳ ቀበሌ በይፋ ተጀምሯል።
ለአንድ ወር በሚቆየው በዚሁ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በወረዳ ደረጃ ከ7ሺህ 3መቶ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።
በሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ የዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ማብሰሪያ መርሃግብር በወረዳው በሰሜን በሌሳ ቀበሌ በ “ዶያንቾ” ንዑስ ተፋሰስ በይፋ ተጀምሯል።
በማብሰሪያ መረሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የሌሞ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢዮብ ጩፋሞ በአፋርና ውሃ ጥበቃ ስራ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ስለመሆኑ ገልፀው ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
አርሶ አደሩ የሰው ጉልበት እንዳይባክንና መሬት ለተጨማሪ ጉዳት እንደይጋለጥ የባለሙያዎችን ምክር ተከትሎ ለተሰሩ ስራዎች ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ኢዮብ ከቀበሌ ጀምሮ ያሉ ባለድርሻ አካለትም በልዩ ትኩረት መንቀሳቀስ ወሳኝ እንደሆነ አንስተዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራን ማጠናከር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ተግባር እንደሆነም ነው ዋና አስተዳዳሪው የገለፁት።
የሌሞ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ምክትልና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ደገፋ አቢዮ በወረዳ ደረጃ በዘንድሮ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በ33 ንዑስ ተፋሰሶች 7ሺህ 3 መቶ 9 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
ከ40ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ለአንድ ወር እንደሚቆይ በተገለጸው በዚሁ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግም ባሻገር ለወጣቱ ክፍል የስራ ዕድልን ለመፍጠር ታስቦ የተጀመረ እንቅስቃሴ ስለ መሆኑም ነው አቶ ደገፋ ያስረዱት።
አርሶ አደሩ በተፈጠረለት ግንዛቤ በቁጭት መንፈስ ወደ ተግባር መግባቱን የጠቆሙት ሀላፊው በዚህም የሴቶች ተሳትፎ እየጨረ ስለ መምጣቱ አንስተዋል።
በዘርፉ የተፈለገውን ውጤት ለማግኘትም አርሶ አደሩ የተሰሩ ስራዎችን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በመጠበቅ ሀላፊነቱን እንዲወጣም ሀላፊው አሳስበዋል።
ወ/ሮ ከድጃ ኑረዲን፣ አስፋው ወልዴ እና ወጣት ሙሉጌታ መኪሶ በማብሰሪያ መርሃ-ግብር ላይ ተሳታፊ የነበሩ የሰሜን በሌሳ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በአከባቢያቸው ላይ ከተጀመረ ወዲህ በአፈር ለምነትም ይሁን በምርት እድገት ላይ አበረታች ለውጦችን መመልከት መቻላቸውን ተናግረዋል።
ከተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እያገኙ እንደሆነ የገለጹት አርሶ አደሮቹ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን አጠናክሮ እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሚባክነውን የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለጸ
ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፈን ጥምር ደን መጠበቅ፣ ማስፋትና መጠቀም እንደሚገባ ተጠቆመ
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማዘመን የዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ