ሀዋሳ፡ የካቲት 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኮሬ ዞን የኬሌ ከተማ አስተዳደር የ2016 የተፋሰስ ልማት ሥራን በይፋ አሰጀምሯል፡፡
ነዋሪዎች የከተማዋን ሕልውና እና ያለውን ሀብት ንብረታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ተራራውን ማልማት እንዳለባቸው በኮሬ ዞን የኬሌ ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።
የኮሬ ዞን መዲና ኬሌ ከተማ በሠንሰለታማ ተራሮች የተከበበች ስትሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተራሮቿ እየተራቆቱ እንደሆነ ነዋሪዎቿ ይናገራሉ።
የ2016 ተፋሰስ ልማት ሥራን ያስጀመሩት የኬሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዮሐንስ ኃይሉ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የምግብ ዋስትናን ከማስጠበቅ ባሻገር ለከተማዋ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ነዋሪዎች የከተማዋን ህልውና ለማስጠበቅ እና ሀብት ንብረታቸውን ከጎርፍ እና ናዳ ለመጠበቅ ሲሉ የተፋሰስ ልማትን በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በ2015 በተሰራው የተፋሰስ ልማት በከፊል ለውጥ እየታየ እንደመጣና ከተንከባከቡ ሰፊ ለውጥ ማየት እንደሚቻልም አመላክተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰመረ አባተ በበኩላቸው፣ የዘንድሮ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በወጣቶች፣ በከተማ ማህበረሰብ እና በመንግስት ሰራተኞች አደረጃጀት እየተሠራ ነው ብለው፣ ከዚህ በፊት የለሙት ውጤት እንዲያሳዩ ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተፋሰስ ልማት ሥራ ላይ ተሳታፊዎች መካከል አቶ በዛብህ ቦጋለ፣ ጀንበሩ ጀጎ እና ባይዛር ባንድራ በሰጡት አስተያየት ሀገር የሚታድገው በጋራ የተፈጥሮ ሀብታችንን ስንጠብቅ ነው ብለዋል።
ያሉንን ረጅም እና ሰንሰለታማ ተራራን ማልማት ለቱሪዝም ዘርፍ ምቹ መደላደልን ይፈጥራል ያሉት ተሳታፊዎቹ፣ ከብቶችን በውስጡ ባለመልቀቅ እና ደኖችን ባለመቁረጥ መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ