ባለፉት አመታት እንደ ሀገር በርካታ ችግሮች የገጠሙ ቢሆንም ዘርፈ ብዙ ስኬቶችም መመዝገባቸው ተገለፀ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበራዊ ክላስተር የመንግስት ሰራተኞች ስልጠና በወራቤ ከተማ ተጀምሯል።

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ሀላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ፤ ባለፉት አምስት አመታት በኢትዮጵያ በርካታ ውጣ ውረዶች ቢኖሩም ከዚሁ ጎን ለጎን በበርካታ ዘርፎች ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያገኙ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመልክተዋል።

የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የስንዴና የልማት ትሩፋትና መሠል ዘርፎች በውጤታማነት የዘለቁ ናቸው ብለዋል አቶ ገብሬ።

ከዕዳ ወደ ምንዳ በሚል ርዕስ እየተሰጠ ያለው ስልጠና በሁሉም አካባቢዎች በየደረጃው እየተሰጠ ስለመሆኑ ጠቁመው ሰላምና ልማት እንዲሁም መልካም አስተዳደር የስልጠናው ማጠንጠኛ ነጥቦች ናቸው ብለዋል።

የሀገሪቱን መንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ በአግባቡ የተረዳ የመንግስት ሰራተኛ መፍጠርና ህብረተሰቡን በአግባቡ እንዲያገለግሉ ማስቻል ደግሞ የስልጠናው ግብ ነው ብለዋል።

በሁሉም ዘርፎች የተሰማሩ ዜጎች የግልና የጋራ ግዴታቸውን በመወጣት ለሃገራዊ ብልፅግና የበኩላቸውን እንዲወጡም አቶ ገብሬ ጥሪ አቅርበዋል።

ለስልጠናው የተዘጋጁ ጥናታዊ ሰነዶች ቀርበው ሰፊ ውይይት እንደሚደረግባቸው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በዚህ ስልጠና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መቀመጫቸውን በወራቤ ከተማ ያደረጉ የትምህርት፣ የጤና፣ የፐብሊክ ሰርቪስ፣ የሴቶችና ህፃናት እንዲሁም የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቢሮ የስራ ሀላፊዎችና ሰራተኞች እየተሳተፉ ነው።

ዘጋቢ፡ ጀማል የሱፍ