ሀዋሳ፡ የካቲት 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) መንግሥት የአከባቢን ቋንቋን ለማበልጸግ በሚያደርገው ጥረት የሃይማኖት ተቋማት ሚናቸውን ሊጫወቱ እንደሚገባ የኮንሶ ዞን አስተዳደር ገለፀ።
ወደ በኮንሲኛ ቋንቋ የተተረጎመ መጽሐፍ ቅዱስ በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ ለምረቃ በቅቷል።
በመጽሐፍ ቅዱሱ ትርጉም ሥራ ላይ ከተሰማሩ የሃይማኖት ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ወንገላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ አንዷ ስትሆን ከ1966 ዓ.ም አንስቶ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኮንሲኛ ቋንቋ እየተረጎመች ቆይታለች።
ቤተ ክርስቲያንቱ በሳባ ፊደላት ያሳተመችው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ በ1994 ዓ.ም ለምረቃ በማብቃት ከ18 ዓመታት በኃላ በላቲን ፊደላት የተፃፈ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ለምረቃ አብቅታለች።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይና የካራት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ፍሬዘር ኮርባይዶ ለምረቃ የበቃው መጽሐፍ ቅዱስ፤ የኮንሲኛ ቋንቋን ለማልማት የሚደረገው ሂደት አጋዥ ከመሆኑም ባሻገር መልካም ሥነ ምግባር ያለውን ዜጋ ለመፍጠርም ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ወንገላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ቋንቋዎችን ከማልማት ባሻገር ሁለንተናዊ ለውጥን ማምጣት የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ለማህበረሰብ አገልግሎት እንደሚተጋ የኢትዮጵያ ወንገላዊት ቤተ-ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ ሲኖዶስ ዋና ፕሬዝደንት ወንጌላዊ ጌታቸው ገሌቦ ተናግረዋል።
የኮንሲኛ መጽሐፍ ቅዱስ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ እንግዳ ኩሲያ የትርጉም ሥራው በብዙ የተለፋበትና በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተሳተፉበት እንደሆነ ተናግረዋል።
አክለውም ማህበረሰቡ በተለያዩ አማራጮች መጽሐፉን ማንበብ እንዲችል ከላቲን በተጨማሪ በሳባ ፊደላት ሙሉውን መጽሐፍ ለማሳተም ውጥን መያዙን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡ አማሮ አርሳባ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ