በአሠራር ከሚተሳሰሩ ተቋማት ጋር የሚደረግ ቅንጅታዊ ሥራ የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ እንደሚሠራ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ የካቲት 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአሠራር ከሚገናኙ መሥሪያ ቤቶች ጋር የሚደረግ ቅንጅታዊ ሥራን በማጠናከር ለተገልጋይ እርካ እንደሚሠራ የአሪ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል።
ዜጎች ጥራት ያለው ፍትህ ማግኘት እንዲችሉ በዘርፉ ያሉ ተቋማት በልዩ ትኩረት መሥራት እንዳለባቸው ተመላክቷል።
የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2016 ዓ/ም የግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ከወረዳና ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች፣ ከህዝብ ክንፍና ባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረግ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የኣሪ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ ሽመልስ እንደገለፁት፥ በዞኑ ስር ያሉ ፍርድ ቤቶች ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠልና የፍትህ ሥርዓቱ ጠንካራና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ እንዲሆን ለማድረግ መሥራትን ይጠይቃል።
ችግሮችን ተወያይቶ መፍታትና ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራርን መዘርጋት ለዘርፉ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ።
በጊዜያዊነት በማረሚያ ቤት ቆይተው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ የሚደረጉ መዝገቦች በአግባቡ በፍርድ ቤት በኩል መመልከትና ውሳኔ ከመስጠት እንዲሁ ማዘገየትና ትኩረት አለመስጠት በተወሰነ መልኩ ክፍተት መኖሩን አቶ አለማየሁ ጠቅሰው ይህ ሙሉ በሙሉ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል።
የመንግስትን ሀብትና ንብረት በሀላፊነት ከመጠቀም አኳያ ሰፊ ችግር እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፥ አንዳንድ የንብረት መጥፋት ችግሮችን ለመለየት የሚያስችል መረጃ እየተጣራ እንዳለ ገልፀዋል።
በመድረኩ ጠቃሚ አስተያየቶች መሰጠቱን የገለፁት የኣሪ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አንተነህ በላይ፥ በፍትህ ዘርፍ ያሉ ተቋማት በጋራና በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ለተገልጋዩ ምቹ ችሎቶችን በመስጠት ወደ ዘመናዊ አሠራር መግባት ከሁሉም መዋቅሮች ይጠበቃል ሲሉም አቶ አንተነህ አሳስበዋል።
“ህዝብን እናገለግላለን ብለን ከተሰየምን በተሰጠን ኃላፊነት ልክ ሰርተን ማርካት አለብን” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የተገልጋይ ቀጠሮ መብዛት፣ የዳኝነት ውሳኔ አሰጣጥ ጥራት መጓደል፣ በሁሉም ፍርድ ቤት ተቋማት ወጥ የሆነ አፈፃፀም አለመኖር፣ የበጀትና የተሽከርካሪ እጥረት የሚሉና ሌሎችም በከዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኩል በበጀት ዓመቱ ግማሽ ወራት ወቅት የታዩ ችግሮች ናቸው ተብለው ተለይተዋል።
ለፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ የኪስ መዝገቦች ወቅቱን የጠበቀ ውሳኔ እንዲሰጥ ማስረጃዎች በተደራጀ መልኩ እየቀረበ አለመሆን፣ የፍትህ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ክፍተት መኖር የሚሉና መሰል ምክንያቶች በፍርድ ቤቶች የውሳኔ አሳጣጡ ማዘገየት ማነቆ ሆኖ ቀርቧል።
ውሳኔ የተሰጠባቸው ጉዳዮች አፈፃፀም ሂደት መዘገየት፣ የወንጀል ጉዳዮችን በአግባቡ አጣርቶ የህግ የበላይነት የማረጋገጥ በኩል ያለ ክፍተት፣ በዕርቅ ሊያልቁ የሚችሉ ጉዳዮች በግንዛቤ እጥረት ወደ ፍርድ ቤት መውስድ ችግር መኖሩ በተሳታፊዎች በኩል ቀርቦ እንዲስተካከል አስተያየት ተሰጥቶበታል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ