የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የመሬት ለምነትን በማሳደግ ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የመሬት ለምነትን በማሳደግ ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል።

በቀቤና ልዩ ወረዳ የ2016 ምርት ዘመን የተፋሰስ ልማት ስራ የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በሌንጫ ቀበሌ  በይፋ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያው መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኑ ሻቡዲን  የተፋሰስ ልማት ስራ ለም አፈር በጎርፍ፣ በንፋስ እና በዝናብ ታጦቦ እንዳይወሰድ ለመከላከልና የአፈር ለምነት ተጠብቆ እንድቆይ ከማድረግ ረገድ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

የአርሶ አደሩን የእርስ በርስ ግንኙነት በማጠናከር በአካባቢያዊና ሀገራዊ የልማት ጉዳዮች ላይ ለመመካከር እድል የሚፈጥርለት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብድልሽኩር ደሊል በበኩላቸው በልዩ ወረዳው በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ስራ በ23 ንዑስ ተፋሰስ  ከ6ሺህ   1መቶ በላይ ሄክታር መሬት እንደሚለማ ጠቁመዋል። በዚህ ስራ ከ25ሺህ በላይ የህረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉም ተገልጿል።

ለተከታታይ 25 ቀናት በሚቆየው በዚህ የተፋሰስ ልማት ስራ የልዩ ወረዳው የህብረተሰብ ክፍሎች በነቂስ በመሳተፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አቶ አብድልሽኩር መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የልዩ ወረዳው ብልጽግና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ካፍ አረቦ በበኩላቸው የተፋሰስ ስራ ወጤታማ እንዲሆን በህብረተሰቡ ዘንድ የታየው ተነሳሽነት የሚደነቅ እንደሆነ አንስተው ለቀጣይ ትውልድ የተሻለ አካባቢን ለማውረስ ሁሉም አካላት የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

የግብርና ስራ ለሀገራችን የጀርባ አጥንት እንደሆነ በመጠቆም ስራው ውጤታማ እንዲሆንም የተፋሰስ ልማት ስራ አስፈላጊ በመሆኑ የተፈጥሮ ሃብት የሆነውን መሬት መንከባከብ የውዴታ ግዴታ መሆኑን አመላክተዋል።

ባለፉት አመታት ባከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ምርትና ምርታማነታቸው ማደጉንና ምንጮች መጎልበታቸውን አስተያየታቸውን ያጋሩን የዘመቻው ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በተሰሩ ስራዎች ላይ የበኩላቸውን አስተዋዕኦ ማበርከታቸውን አስታውሰው ለሚቀጥሉት 25 ቀናት በሚቆየው የዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ስራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን