የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክርቤት 4 የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን አጸደቀ

ሀዋሳ፡ የካቲት 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክርቤት በክልሉ ተፈፃሚ የሚሆኑ 4 የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን አፅድቋል፡፡

የምክር ቤቱ 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬም በሁለተኛ ቀኑ የተለያዩ አዋጆችን በማጽደቅ ቀጥሏል።

ለምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጆችን ያቀረቡት የክልሉ ምክርቤት የህግ፣ ፍትሕና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ንጉሴ ወ/ጊዮርጊስ፥ ረቂቅ አዋጆቹ የሀገሪቱ ህገመንግስት በሚፈቅደው መሠረት በክልሉ በሚፀሙ ጉዳዮች ዙሪያ የተዘጋጁ መሆናቸውን አብራርተዋል።

አስፈላጊነታቸውም ክልሉ በዘርፎቹ የራሱ የሆነ አዋጅ እንዲኖረው ለማስቻል መሆኑን ጠቅሰው፥ የወጡ አዋጆችም የክልሉ የገጠር መሬት መጠቀሚያና የግብርና ስራ ገቢ ግብር አዋጅ፣ የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ፣ ይቅርታ አሰጣጥ አዋጅ እና የአካባቢ ማሟያ ምርጫ  አዋጆች ናቸው።

4ቱም ረቂቅ አዋጆች በቋሚ ኮሚቴ ታይተውና ተጣርተው የቀረቡ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በአዋጁ ዙሪያ ሀሳብ ያቀረቡ የምክር ቤቱ አባላትም በተጠቀሱ ጉዳዮች በተለይም በክልሉ ያለውን የመሬት ሀብትን በአገባቡ መጠቀም እንዲቻል አዋጅ መውጣቱ የጎላ ጥቅም እንዳለው እንስተዋል።

አዋጆቹ በተብራራ መልኩ እስከታችኛው መዋቅሮች ግልፀኝነት መፈጠር እንደሚገባና አባላቱ አስተያየት  ሰጥተዋል።

የክልሉ ግብርና እና የገቢዎች ቢሮ ኃላፊዎች ከአባላቱ በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የመሬት መጠቀሚያና ገቢ ግብር አዋጅ በክልሉ ካለው የመሬት ሀብት በተገቢው ለመጠቀምና በዘርፉም ገቢ ለማግኘት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባህር ዛፍና ጫት ላይ ገቢው መጨመር የተቻለውም ካለው ጥቅምና ጉዳት እንዲሁም አስፈላጊነታቸውን ጥናት ውስጥ በማስገባ መሆኑንም አብራርተዋል።

4ቱም ረቂቅ አዋጆች ተፈፃሚ እንዲሆኑ በምክርቤቱ አባላት ሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን