ሀዋሳ፡ የካቲት 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ በተያዘው በጀት አመት በክልሉ 84 ሚሊዮን የእንሰት ችግኞችን ለመትከል አቅዶ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።
እንሰት የሚያበረክተውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ከግምት በማስገባት ተክሉን ለማልማት በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም የባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው ተገልጿል::
እንሰት በተለያዩ አካባቢዎች በስፋት የሚለማ የተክል አይነት መሆኑ ተጠቁሟል።
በተለይም በደቡብ፣ በማዕከላዊና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በስፋት የሚለማ ሲሆን በእነዚህ አካባቢዎች የኢኮኖሚ ጠቀሜታው እጅግ ከፍተኛ ነው ያሉት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ር/ማስተዳደር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባበሪና ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር፥ እንሰት ለምግብነት፣ ለባህላዊ መድሃኒት፣ ለመኝታ ለልብስና ለሌሎችም አገልግሎቶች መዋል የሚችልና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን የሚሰጥ በመሆኑ በማልማትና በመንከባከቡ ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል ።
ለምግብነት የሚሰጠው አገልግሎት ሲታይ በሀገር ውስጥ ለምግብ ፍጆታ ከመጥቀም ባሻገር በቆጮ ላይ እሴት በመጨመር ባለፈው አመት ውጭ ሀገር በመላክ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት የተቻለ መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው፥ ድርቅ በሚያገጥምበት ወቅት ድርቅን የመቋቋም አቅም ስላለው የሰው ልጅን ከራሃብ የሚታደግ እንደሆነም ገልጸዋል።
በክልሉ በተያዘው በጀት አመት 84 ሚሊዮን የእንሰት ችግኞችን ለመትከል ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን አተካከሉንም በተመለከተ ከዚህ ቀደም ከሚተከልባቸው አከባቢዎች ይበልጥ ቆላማ በሆኑ አከባቢዎች በብዛትና በጥራት የሚተከል መሆኑንም ጠቁመዋል።
የእንሰትን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከተለመደው የማምረት ዘዴ ተላቀን በዘመናዊ መንገድ ማልማት፣ በሽታውንም ለመከለከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የግብርና የምርምር ማዕከላት በጋራ ተቀናጅተው ከሰሩ ከእንሰት የሚፈለገውን ጥቅም ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል።
በአርባምንጭ ዩንቨርሲቲ ምሁራን አማካኝነት በአዲስ ቴክኖሎጂና ሀገር በቀል እውቀትን በመጠቀም በአጭር ግዜ ውስጥ የእንሰት ውጤትን በዱቄት መልክ በማዘጋጀት ታሽጎ ለገበያ በማቅረብ ለኬክ፣ ለቺፕሥና ለሌሎችም ቀደም ሲል ላልተለመዱ የምግብ አይነቶች መዋል የሚችል የተክል አይነት መሆኑንም አመላክተዋል::
ዘጋቢ፡ ናስር ጀማል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ