በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ ነፍሰጡር እናቶች ድጋፍ ተደረገ

በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ ነፍሰጡር እናቶች ድጋፍ ተደረገ
‎
‎ድጋፉ በኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ፣ ጤና ሚኒስቴር እና በክልሉ ግብርና ቢሮ ማቺንግ ፈንድ ሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም ጋር በመተባበር እንደሆነም ተጠቁሟል
‎
‎
‎በዞኑ ሎማ ቦሳ ወረዳ ግብርና አከባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት ከሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነት በተገኘው ገንዘብ ድጋፍ ከቦሳ ሾጋ፣ ቦሳ ፀደፋ፣ ቱላማ ጣማ እና ከኤላ ባቾ ቀበሌያት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ 55 አጥቢና ነፍሰ ጡር እናቶች ድጋፍ አድርጓል።
‎
‎በሰቆጣ ቃልኪዳን የሚከናወኑ ተግባራት በወረዳው የህጻናትን የመቀንጨር ምጣኔ ለመቀነስ ጉልህ አስተዋጽኦ እየተወጣ እንደሚገኝ የተናገሩት የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ አስፋው ቦሎላ ናቸው ።
‎
‎እንደ በአስተባባሪው ገለጻ ህብረተሰቡ ቤት ያፈራዉን በአግባቡ አዘጋጅቶ እንዲመገብ፣ ከኋላቀር የልጆች አስተዳደግ ባህልና ልምድ እንዲላቀቅ ፣ እናት በእርግዝና ወቅት በቂ ምግብ እንድትመገብ ፤ ከወልድም በኋላ ጡት በበቂ መጠን እንድታጠባ እና ከ6 ወር በኋላ ተጨማሪ ምግብን ህፃኑ እንዲጀምር የግንዛቤ ማስጨበጭያ ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
‎
‎ የጨቅላ ህፃናትን መቀንጨር ለመከላከል እና በዚህም ሳቢያ ሊመጣ የሚችለውን ሞት ለመቀነስ የወተት ላም ፣ በግና ፍየል ግዢ በመፈጸም ስርጭት እያደረጉ እንደሚገኝም አብራርተዋል ።
‎
‎
‎
‎ድጋፍ የተደረገላቸው እናቶችም በበኩላቸው፣ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመሰግነው በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ተግተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
‎
‎ዘጋቢ ፡ አሸናፊ ግዛው – ዋካ ጣቢያችን