በክልሉ ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት የአስፈፃሚ አካላት የ6 ወራት ሪፖርት በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
በሪፖርቱ ዙሪያ አባላት ባቀረቡት ጥያቄ ዙሪያ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጋሾ በክልሉ የመሰረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት በክልሉ መንግስት በጀት የተቻለውን ያህል እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው በዘርፍ በህብረተሰብ ድጋፍ የሚሰሩት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ክልሉ የገጠመውን የበጀት እዳ ለመሸፈን ያለውን በጀት ቆጥቦ በመጠቀምና እዳዎችን በመቀነስ የተሻለ ተግባር ስለመፈፀሙ አብራርተዋል።
የግብርናውን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በስንዴ፣ በጓሮ አትክልት እና ቡና ልማት ዘርፍ የተሻለ ምርት ማግኘት መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል።
ቢሆንም የግብአት ገንዘብ በጊዜ ከማስገባት ረገድ አሁንም የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውን አንስተው በተዋረድ ያሉ አካላት መዋቅሮቻቸውን መፈተሽ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በክልሉ የምርጥ ዘር እጥረትን ለመቅረፍ አምርቶ ለመጠቀም በኮንታ ዞን በተጀመረው የምርጥ ዘር ብዜት ውጤታማ ምርት ማግኘት መቻሉን ተናግረው በዘርፉ ይበልጥ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።
ምርቶችን ወደ ገበያ ለማቅረብም የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮች ማነቆ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት የአርብቶአደር አካባቢዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዋል።
የትምህርትና መንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽነትን ለማሳግ በህብረተሰቡ የተደረገው ድጋፍ የሚያስመሰግን መሆኑን አንስተዋል።
የሚነሱ በርካታ የልማት ጥያቄዎችን በውስን የመንግስት በጀት ብቻ መሸፈን ስለማይቻል የህዝብ ተሣትፎን አጠናክሮ መሄድ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጋሾ ገልፀዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ወንድሙ ኩርታ ከአባላት የተነሱ ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ የከተሞችን ደረጃ ከማሻሻል፣ በትምህርትና ጤና ተቋማት የሚመደቡ በጀቶች አጠቃቀምን ለማሻሻልና የእናቶችና ህፃናት የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን በሚመለከት የቀጣይ የትኩረት መስኮች መሆን እንዳለባቸው አሳውቀዋል።
የክልሉ 6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት በምክር ቤቱ የተለያዩ ሀሳብና አስተያየቶች ቀርበው በአባላቱ ሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ