ፅዳትን ባህል ማድረግ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)

ፅዳትን ባህል ማድረግ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)

ፅዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የአመለካከት ለውጥ ሊመጣ ይገባል ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ማስተማርና ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

ስራዎች ከሰሩ መስቀል አደባባይን የመሰሉ አከባቢዎች ላይ የመጣው ለውጥ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

በግለሰብ ደረጃ መቆሸሽ ነውር ተደርጎ መወሰድ አለበት ያሉት ዶ/ር እንዳሻው ፅዳትን በሌላ በኩል ዘመናዊነት ማሳያ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ከተሞችን አረንጓዴ የማድረግ ሂደት ላይ ገና ብዙ መስራት ይጠበቃል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ
ፅዳትን ዕምነት በማድረግ ወደ ባህል መቀየር ያስፈልጋል ለዚህም ተከታታይነት ያለው ስራ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡

የኢፌዴሪ አከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሚ የአየር ብክለት ግንዛቤ ለውጥ በማምጣት ፅዳትን ባህል ለማድረግ የሚያስችል ስራ እንደሚሰራ ገልፀዋል። ከማስተማር ባለፈ ብክለት ፈጣሪ ግለሰቦችና ተቋማት በህግ ይጠየቃሉ ብለዋል።ጥሩ የሰሩትን ማበረታታት እና አረንጓዴ አሻራን ማኖር ጎን ለጎን ይከናወናል ፡፡

በፅዳት ሞዴል የሆኑ ከተሞችን መፍጠር ተችሏል ያሉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና ኢንዱስትሪ ዘርፍ አስተባባሪ የክልሉ ከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ ስንታየሁ ወልደሚካኤል ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ሌላ ሃብት መፍጠር መቻሉን አንስተዋል።

የክልሉ ደንና አከባቢ ጥበቃ ቢሮ ሃላፊ አብርሃም መጫ የአየር የውሃና የአፈር ብክለትን ለመከላከል የሚያስችል ስራ ለመስራት ዕቅድ መያዙን ጠቅሰው በቀጣይ ስድስት ወራት ገቢራዊ ይሆናል ብለዋል።
የቄራ አከባቢ ብክልትን መከላከል ላይ ጉድለት መታየቱን ያነሱት ሃላፊው በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል ፡፡

የአከባቢ ብክለት ላይ ተጨማሪ ችግር እየፈጠረ ያለው ጉዳይ የፖለቲካ ብክለት እንደሆነ ያነሱት የክልሉ መንግስት ዋና የመንግስት ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር) የሃሰት መረጃ በማሰራጨት ፖለቲካዊ ብክለት እየተፈጠረ ነው ብለዋል ፡፡ ይሄን ለማረቅ ድግሞ የሚዲያ ተቋማትና እና አንቂ ግለሰቦች የሚፈጠሩ የውሸት ብክለቶችን በእውነተኛ መረጃ ማከም አለባቸው ብለዋል ፡፡

ዘጋቢ:ሲሳይ ደበበ