“ውጤት ካለጥረት አይገኝም” – አቶ ጌታቸው መጋቦ

በደረሰ አስፋው

“በአካባቢው ትምህርት ጨርሼ ስሸከምና ሳርስ በሰዎች ዘንድ የተደበላለቁ ስሜቶች ይስተዋሉ ነበር፡፡ አንዳንዶች ያሾፉብኛል፤ ሌሎች ደግሞ ያደንቁኛል፡፡ ይሁን እንጂ ተማርን ብለው አፈር አይንካን ላሉት አስተማሪ መሆን ችያለሁ፡፡ ስራ ጠባቂ የሆኑትን ለስራ አነሳስቻለሁ፡፡ ከተቀጣሪነት ይልቅ ሰርቶ መለወጥ ይቻላል የሚለውን አስተሳሰብ እንዲኖራቸው አድርጌያለሁ፡፡ እራስን ዝቅ አድርጎ ከሰሩ መለወጥ አይቀርም” ሲሉ የገለጹልን ታታሪው ባለታሪካችን ዛሬ ለደረሱበት ለውጥ ብቸኛው ሚስጢር ስራ ብቻ እንደሆነ ነው የገለጹልን፡፡

አቶ ጌታቸው መጋቦ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ከጠምባሮ ልዩ ወረዳ ርዕሰ ከተማ ሙዱላ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ዱርጊ ቀበሌ ነው፡፡ ከአባታቸው ሞት በኋላ ግን እናታቸው ጋር ወደ ጉና ወረዳ ሲሄዱ እሳቸውም ዱርጊን ለቀው መኖሪያቸው ዱና አደረጉ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ቦጋ 1ኛ ደረጃ፣ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ ግምቢቾ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡

በጊንቢቾ ሲማሩ ግን ከባድ የሚባለው ፈተና ተጋፍጠው ነው፡፡ የ3 ሰዓት የእግር መንገድ ስንቅ ተሸክመው በመጓዝ ነበር የተማሩት፡፡ ከሰኞ እስከ አርብ የሚያደርሳቸውን የበሰለና ያልበሰለ ስንቅ በመሸከም ነበር የሚጓዙት፡፡ በዚህ ሁሉ ችግር ግን የ12ተኛ ክፍል ትምህርታቸውን በስኬት አጠናቀቁ።

ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ሌላ ሀገራዊ ኃላፊነትን መወጣትም ግድ አላቸው፡፡ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ አገልግሎት፡፡ የ12ኛ ክፍል ውጤት እስኪመጣ ወደ ገጠሩ የማህበረሰብ ክፍል ዘልቀው የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል። ፊደል አስቆጥረዋል፡፡ ለአርሶ አደሩ ዘመናዊ እርሻን፣ ለህዝባቸው የዘመናዊ አኗኗር ዘዴን አስተምረዋል፡፡ በዚህ ሁሉ እርካታን እንዳገኙበት ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ታላቅ የሆነ ሀገራዊ ስሜት የሚንጸባረቅበት፣ ሀገርን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ለማላቀቅ በእልህና በቁጭት የምትሰራበት በመሆኑ ስሜቱ የተለየ ነበር ሲሉ ነው የዘመቻውን ትዝታ የገለጹት፡፡

የቤተሰቡ አምስተኛ ልጅ የሆኑት ባለታሪካችን ሌሎች ታላላቅ ወንድሞቻቸው ከአካባቢው ራቅ ያሉ በመሆኑ የቤተሰቡ ሀላፊነትም በእሳቸው ላይ የወደቀ ነበር፡፡ የእናታቸው ብቸኛ ጠዋሪ እና ረዳት ነበሩ፡፡ የአርሶ አደር ልጅ እንደመሆናቸው ትምህርት እየተማሩም ሆነ በመሰረተ ትምህርት ዘመቻው እየተመላለሱ የቤቱ የእርሻ ስራ እንዳይስተጓጉል ያደርጉ ነበር፡፡ ይህ ታታሪ ሰራተኝነታቸው ለዛሬው መለወጣቸው መሰረት እንደሆናቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ከመሰረተ ትምህርት ዘመቻው በኋላ የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው መጣ፡፡ ውጤቱ አስደሳች ቢሆንም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መግባቱን ግን ትኩረት አልሰጡትም፡፡ ከትምህርቱ ይልቅ ወደ ንግዱ ነው ያዘነበሉት፡፡ ከንግዱ ጎን ለጎንም የእርሻ ስራውን ተያያዙት፡፡ በዚህ መሀል ግን አንድ አዲስ ክስተት ተከሰተ፡፡

የእርሻ ስራ እየሰሩ ገዝተው ያሞከቱትን በግ ነበራቸው፡፡ ይህን በግም በ200 ብር ሸጡ። ይህ ብር በኪሳቸው እያለ በ1983 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ወንድማቸውን ሊጠይቁ ሄዱ፡፡ በአዲስ አበባም ወደ መርካቶ ጎራ ማለታቸው አልቀረም፡፡ ልባሽ ጨርቆች በቅናሽ ዋጋ ሲቸበቸብ ተመለከቱ፡፡ ወደ አካባቢያቸው ቢወስዱ ትርፋማ እንደሚያደርጋቸው አሰቡና እሳቸውም በግዥው ተሳተፉ፡፡ በኪሳቸው የነበረችውን 200 ብርም በዚሁ ላይ አዋሉት፡፡

ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው በገበያ ላይ በመሸጥ ትርፋማ ሆኑ፡፡ ትርፉ ዳጎስ ያለ ስለነበር ወደ አዲስ አበባ ተመላልሰው የልባሽ ጨርቁን ንግድ አጧጧፉት፡፡ ንግዳቸውም አድማሱን አስፍቶ ከጊምቢቾ አለፎ የገጠርና ከተማ ገበያዎችን አዳረሱ፡፡ እስከ 3 ሰዓት የሚወስድ የእግር መንገድ ልብሶችን ተሸክመው በመሄድ ይሸጡ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡

ታታሪው ባለታሪካችን በሂደት ድካማቸውን ለመቀነስ የጭነት ፈረስ በመከራየት መስራት ጀመሩ፡፡ የኪራይ ፈረስም አዋጭ አለመሆኑን ተረዱ፡፡ ለአንድ ቀን ውለው ካደሩ የ2 ቀን ክራይ እንዲከፈል የአካባቢው የኪራይ ህጉ ያስገድዳልና ተከታታይ ቀናትን የመቆየት አጋጣሚ ስለነበር ኪራዩን አበዛባቸው፡፡ ንግዱን በጀመሩ በ3 ወር ዕድሜ አንድ የጭነት ፈረስ በ260 ብር ገዙ፡፡

የእግር መንገድ ሲጓዙ ለበርካታ ጊዜ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ሸጠው የሚያገኙትን ሁሉ የዘረፏቸውን ቀንም አልዘነጉትም፡፡ በአንድ ወቅት የገዙትን ፈረስ ወዳጅ መስሎ የቀረባቸው “ደከመኝ ትንሽ መንገድ በፈረሱ ልሂድ” በማለት ፈረሳቸውን በሽምጥ ጋልቦ እብስ ያለውንም ሌባ ዛሬም ድረስ ከህሊናቸው አልተሰወረም፡፡ በሌላም ጊዜም እንዲሁ ዘራፊዎች መሳሪያ ግንባራቸው ላይ ደግነው 1 ሺህ 700 ብር የዘረፏቸውንም ያስታውሱታል፡፡

ይሁን እንጂ በሚያጋጥማቸው ችግር ተስፋ አልቆረጡም፡፡ ችግሩ ያልፋል፤ ስራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በመሰናክሎች ስራቸው አንድም ቀን እንዲስተጓጎል እድል አይሰጡትም፡፡ እንዲያውም ከልባሽ ጨርቆች በተጨማሪ አዳዲስ ልብሶችን ጭምር ለሺያጭ ማቅረብ ጀመሩ፡፡

የአቶ ጌታቸው ካፒታልም ከፍ እያለ መጣ፡፡ ከንግዱ አለፍ ብለው መሬት እየተኮናተሩ በእርሻ ስራም ተሰማሩ፡፡ ምርት በሚሰበሰብበት ወቅትም እህል ገዝተው በማስቀመጥ አትርፈው በመሸጥ ትርፋማ ሆኑ፡፡ ከብት በርካሽ ገዝተውና አደልበው በመስቀል በዓል ወቅት ይሸጣሉ፡፡ ንግዳቸውን ከጀመሩበት ከ1983 ዓ.ም እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ በርካቶች ረጅም ጊዜ ሰርተው ያላመጡትን ለውጥ እንዳመጡ ነው የገለጹት፡፡

የንግድ አድማሳቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ይሄድ ነበር፡፡ ውጤታማ የሚያደርጉ የንግድ ዘርፎችን እያጠኑ ይሰራሉ፡፡ ከሱቁ ጎን ለጎንም ሻይ ቤት ከፈቱ፡፡ የልብስ ስፌት ማሽን ገዝተውና ባለሙያዎችን ቀጥረው በዚህም ዘርፍ ላቅ ያለ ተጠቃሚ ሆኑ፡፡ የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊ አቅም ከማሳደግ ባሻገር ለአካባቢው የስራ ባህልንም በማሳደግ አርያነት ያለው ተግባር ፈጽመዋል። በርካታ የአካባቢው ተወላጆች ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመሄድ መዋለ ነዋያቸውን ሲያፈሱ እሳቸው ግን በአካባቢያቸው ገንዘባቸውን በማፍሰስ ለበርካቶች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡

“የፈጣሪ እገዛ ታክሎበት በአጭር ጊዜ ብዙ ስራ ሰራሁ፡፡ በትራንስፖርት እጦት ህዝቡ ሲንገላታ ተመለከትኩ፡፡ ለዚህም የህዝብ ማመላለሻ መኪና ገዛሁ፡፡ ተሸከርካሪውም ከአንድ ወደ ሁለት ተሸጋገረ፡፡ ህዝቡን ልጥቀም በማለት እንጂ ከተሸከርካሪው እጠቀማለሁ ብዬ አልነበረም። ነገር ግን እኔም ህዝቡም ተጠቃሚ በመሆኑ በሥራው እደስታለው፡፡ እኔ ከስራ ውጭ ልዝናና አላልኩም። አብዛኛውን ጊዜ የማሳልፈው በስራ ነው፡፡ ጊዜን ማበካን አልወድም፡፡”

አቶ ጌታቸው ሌላው የታታሪነታቸው መገለጫ ታናሽ ወንድማቸውን አስተምረው ለቁም ነገር ማድረሳቸው ነው፡፡ ሱቅ ከፍተው ወንድማቸው እንዲሰሩ አደረጉ፡፡ ተደጋግፎ ለማደግ የነበራቸውንም ውጥን አሳክተዋል፡፡ ዛሬ ሁለቱ ወንድማማቾች በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ሙዱላ ከተማ በሆቴል፣ በግብርና እና ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሰማራት በወረዳው እድገት ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ስለመሆኑ መገንዘብ ችያለሁ፡፡ ለሌሎችም ወደ ከተማው መጥተው መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ፈር ቀዳጅ ናቸው፡፡

አቶ ጌታቸው በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ሙዱላ ከተማና አካባቢው በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተዋል፡፡ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ግብአት አቅራቢ በመሆን ምርጥ ዘር፣ ኬሚካል፣ የአፈር ማዳበሪያ እና የተለያዩ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ከአርሶ አደሩ ጋር በቅርበት እየሰሩ ነው፡፡ ለዚህም ነው፡-

“የተፈጠርኩት ከአርሶ አደሩ ማህበረሰብ ነው፡፡ አሁንም ከአርሶ አደሩ ጋር አብሬ መስራት እፈልጋለሁ፡፡ እቅዴም ይሄው ነው፡፡ ሀገር ሠላም ከሆነች ከአርሶ አደሩ ጋር ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እሰራለሁ”፡፡

ሌላው የተሰማሩበት የልማት ስራ የእንስሳት እርባታ ነው፡፡ በወተት ከብቶች እርባታ፡፡ በዚህም በአካባቢው የወተት ምርታቸውን በማቅረብ እራሳቸውንም አካባቢውንም እየጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ በተለይ “ቅድሚያ ለህጻናት” በሚለው መመሪያቸው ወተቱን ለህጻናት እንዲቀርብ እያደረጉ መሆኑን ከተጠቃሚዎችም መረዳት ችያለሁ፡፡

አቶ ጌታቸው በተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች ለ10 ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ሂሳብ ሰራተኛ፣ ስራ አስኪያጅ፣ የጽዳት ሠራተኛ፣ የጥበቃ ሠራተኛ፣ የእንስሳት ሀኪሞች፣ ሰብል ሻጭ፣ የእንስሳት መድሃኒት ሻጭ፣ ሰራተኞቹ የተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉትም፡-

“እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም አብረን እንድናድግ ነው ዓላማዬ፡፡ ለሰዎችም የስራ ዕድል ስፈጥር ዓላማው ስራ በመፍጠር በአካባቢው ገኖ የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር በመቅረፍ አብሮ ለማደግ ካለኝ ውጥን የተነሳ ነው፡፡”

ባለታሪካችን ባለቤታቸው በእንስሳት ጤና ባለሙያነት በወላይታ ሶዶ ተምረዋል፡፡ በዚህ ሙያቸውም ሰራተኞቻቸው ችግር ሲያጋጥማቸው ተክተው መስራት የሚያስችል ዕውቀት በቤታቸው አለ፡፡ ከተቋማቸው ተቀጥረው ልምድ የወሰዱ በርካታ ሠራተኞቻቸው በሌሎች ተቋማት ተቀጥረው ይሰራሉ፡፡ የራሳቸውን የንግድ መስመር የከፈቱም እንዳሉ ነው የተናገሩት፡፡

ከወረዳው መስተዳደር ጋርም በቅርበት ይሰራሉ፡፡ ወረዳው ችግር ባጋጠመው ጊዜ የግላቸውን ተሸከርካሪ በመስጠት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ በግብአት አቅርቦትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ከአርሶ አደሩ ጎን በመሆን ድጋፍ ያደርጋሉ። በተለይ በግብርናው ዘርፍ፡፡

“ሀገሪቷ ገና የምግብ ዋስተናዋን ያላረጋገጠች በመሆኑ በእርሻ ዘርፍ ለመሰማራት ነው ዕቅዴ። መንግስት ለዚህ የሚሆን ሰፊ የእርሻ ቦታ ከሰጠኝ በሰብል ልማት፣ በቅመማ ቅመምና በሌሎች ዘርፎች የመሰማራት ውጥን አለኝ፡፡ የእንስሳት እርባታውንም የማስፋፋት ምኞት አለኝ፡፡ ትራክተሮችን፣ ኮምባይነሮችንና ሌሎችን የግብርና ማሽኖችን በማቅረብ ግብርናው እንዲዘምን፣ አርሶ አደሩም የሜካናይዜሽን እርሻን እንዲጠቀም የማስተዋወቅ ፍላጎት አላቸው፡፡

ዛሬ ላይ ባለታሪካችን ሰርተው ሀብት ፈጥረዋል። በሙዱላ ከተማ ባለ ሶስት ወለል ህንጻ ገንብተዋል። ለባንኮች ምቹ የስራ አካባቢ እንዲኖር አድርገዋል። የግብርና ማዕከል ገንብተዋል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት ሙዱላ ከተማ ላይ ሰርተዋል፡፡ በተመሳሳይ ከስራቸው ባህሪ የተነሳም ግዙፍ የሆነ መጋዘንም እንዲሁ፡፡ ጥቂቶችን እነዚህን እንጥቀስ እንጂ ስራቸው ከዚህም የላቀ ነው። በተለይ በአካባቢው ላይ ልማት እንዲስፋፋ ያላቸው ተነሳሽነት የሚመሰገን ነው፡፡

“ውጤት ካለጥረት አይገኝም፤ መንግስት የተቸገረው ስራ የለም የሚል መበራከቱ ነው። ስራ የማይወድ ሰው ስራ የለም ነው የሚለው፡፡ እኔ የትኛውንም ስራ እሰራለሁ፡፡ ለዚህ የበቃሁትም ስራን አማርጬ ሳይሆን ሰርቼ ነው፡፡ የቀን ሰራተኛ ቀጥሬ አልቀመጥም፤ አብሬ እሰራለሁ፡፡ ማንም ሰው ከዜሮ ተነስቶ ነው ሀብታም የሚሆነው፡፡ “ያልሰራ አይብላ” ስለተባለ ስራን ባህል ማድረግ ይገባል፡፡”

በማህበራዊ ዘርፍ የሚያደርጉት አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው፡፡ የተለያዩ ባንኮች ሙዱላ ከተማ እንዲገቡ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሙዱላ ከተማ እንዲገባ እስከ አዲስ አበባ በመሄድ ያደረጉት አስተዋጽኦም የማይዘነጋ መሆኑንም ከቅርብ ጓደኞቻቸው መረዳት ችያለሁ። በተመሳሳይ ንብ ባንክ ሙዱላ ከተማ ስራ እንዲጀምር የሳቸው እጅ አለበት፡፡

ወረዳው መልካም የሆነ ነገር እንዲኖር ደከመኝ ሳይሉ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የተጣላውን ያስታርቃሉ፡፡ የተቸገረውን ይረዳሉ፡፡ ህገ ወጦችን ያርማሉ፡፡ የመሰል ባለታሪኮች መበራከት ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነውና ሊደገፍ ይገባል እንላለን፡፡