የሀገራዊ ምክክር መድረክ የታለመለትን ሀገራዊ ዓላማ እንዲያሳካ ህብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሀላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ተመላከተ
ሀዋሳ፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀገራዊ ምክክር መድረክ የታለመለትን ሃገራዊ ዓላማ እንዲያሳካ ህብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሀላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ተመላከተ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ የሚሰጡ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮችን ለመምረጥ የሚያስችለው የውይይት መድረክ ዛሬም በወልቂጤ ከተማ ቀጥሎ ውሏል።
ይህ በአይነቱ ልዩና በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነው ሃገራዊ ምክክር የተፈለገው ውጤት እንዲያመጣ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ነው የተገለፀው።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ እንዳሉት ሀገራዊ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ለችግር የዳረጉትን ምክንያቶች በመለየትና ተገቢውን ምክክር በማድረግ ምክረሃሳቦችን በማሰባሰብና መፍትሄ በመስጠት ነው።
እስካሁንም በተባባሪ አካላት ድጋፍ ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙት የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሰጡትን አጀንዳዎች በማሰባሰብ ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡ ተወካዮች መለየት መቻሉንም ነው የተናገሩት።
ይህ መድረክም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጡትን አጀንዳዎች በማሰባሰብ ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡትን ተወካዮች ከየማህበራዊ መሰረቶቻቸው እንዲመረጡም ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት ነውም ብለዋል።
በመሆኑም ከማህበረሰቡ ክፍሎች ሁለት ሁለት ተወካዮች ከአንዳንድ ተጠባባቂ ጋር እንደሚመረጡም ተገልጿል።
ሂደቱም ተአማኒነትና ትጋትን የሚጠይቅ እንደሆነም ከግንዛቤ መግባት እንዳለበትም ተናግረው ምርጫው በሚካሄድበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎ ሀገራዊ ሃላፊነትን የሚሸከሙ አካላት ሊመረጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም መድረኩ እጅግ አስፈላጊና በጉጉት ሲጠብቁት እንደነበር በመግለፅ እንደሃገር ያሉብንን ችግሮች መንስኤዎቻቸው በመለየትና በጋራ በመምከር ሁሉን አቀፍ የሆነ ሀገራዊ መፍትሄ ያመጣል ሲሉም ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ሲጠናቀቅ እስከ ዛሬ ሳንግባባቸው በቁዮ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ የተሻለችና ለሁሉ እኩል የሆነች ሀገር ትኖረናለች የሚል ተስፋ እንደሰነቁም ነው ተሳታፊዎቹ የገለፁት።
ይህ ትልቅና መሰረታዊ አላማ ያነገበ ኩነት የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቅንነትና በትጋት ሀገራዊ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል ተሳታፊዎቹ።
በዛሬው ውሎ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተወክለው የመጡ ተሳታፊዎች የሚወክሏቸውን አካላት የሚመርጡበትና ለመረጧቸው ሰዎች የአጀንዳ ሃሳብ የሚያካፍሉበት እንደሚሆንም ነው ከመድረኩ መርሃግብር ለመረዳት የተቻለው።
በመድረኩ በ2ኛው ቀን ውሎው የጌቶ፣ የጉመር፣ የቸሃ፣ ወረዳዎች እንዲሁም የአረቅጥ እና የእምድብር ከተማ አስተዳደሮች ተወካዮች እየተሳተፉ እንደሚገኙም ተመላክቷል።
በመድረኩ ላይ ወጣቶች፣ መምህራን፣ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ