አካዳሚው ብቃት ያላቸው መሪዎችን ለማፍራት ዓልሞ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ አስታወቀ

አካዳሚው ብቃት ያላቸው መሪዎችን ለማፍራት ዓልሞ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ አስታወቀ

አካዳሚው ለክልሉ ወጣቶችና ለሴቶች አደረጃጀት አመራሮች በየም ዞን ሳጃ ከተማ እየሰጠ ያለው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እንደቀጠለ ነው።

የአካዳሚው ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የስልጠና ዘርፍ ሀላፊ አቶ አብድልበር ዑስማን ወጣቶቹ ሀገራዊ ተልዕኮን የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ ትልቅ አደራን ተሸክመው የሚንቀሳቀሱ ናቸው ብለዋል።

አካዳሚው እየሰጠ ያለው ስልጠና በአመራሩ ላይ የሚታዩ የአመለካከት ውስንነትን የሚቀርፍበት፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች መኖርን የሚለማመዱበት፣ በአርበኝነት ተልዕኮአቸውን የሚፈጽሙበት፣ አሰባሳቢ ትርክት የሚጸናበት ነው ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብላቱ ያለ ብቁ መሪ እድገትም፣ ብልጽግናም፣ ልማትም ሊታሰብ እንደማይችል ነው የጠቆሙት።

ለሁሉም ለውጦች መሠረቱ መሪዎች መሆናቸውን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ብቃት ያላቸው መሪዎችን ለማፍራት ታሳቢ ያደረገ ስልጠና ነው እየሰጠን የምንገኘው ብለዋል።

የመደመር ትውልድ ብዙ የተመሠቃቀሉ ጉዳዮችን የሚያስተካክል የነገ ራዕይ፣ ትልሞች እና እቅዶችን የሚያቃና መሆኑም አቶ ተስፋዬ ብላቱ ገልጸዋል።


በአካዳሚው ያገኙት ስልጠና ስለ አንድ ጠንካራ አመራር ሊያሟላቸው የሚገቡ እውቀትና ሊያዳብራቸው የሚገቡ ክህሎትን የተገነዘቡበት መሆኑን ሰልጣኞች ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አብደላ በድሩ