ሀዋሳ፡ ጥቅምት 27/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥና ገበያን ለማረጋጋት ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ በንብ እርባታ የተሰማሩ ወጣቶች ተናገሩ፡፡
በዘርፉ በርካታ ወጣቶችን በማሰማራት ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጸው ደግሞ የወረዳው ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽ/ቤት ነው፡፡
አንድነት የወጣቶች ማህበር በወረዳው ኩጢ ቀበሌ በንብ እርባታ ዘርፍ በ10 አባላት በ2012 ዓ.ም የተመሰረተ ማህበር ሲሆን፥ አሁን ላይ የጓሮ አትክልትና የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት ላይ መሆናቸውን የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት አህመድ እሸቱ ተናግሯል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ የገቢ አቅማቸው መሻሻል አስደሳች ለውጥ መሆኑን የሚናገረው ወጣት አህመድ፥ በሚያገኙት ገቢ ቤተሰቦቻቸውን እያሰተዳደሩ ስለመሆናቸውም ይገልጻል፡፡
ወጣት ጥላሁን ሀሰን እና መሃመድ እንድሪስ የማህበሩ አባል በመሆናቸው የተሻለ ሀብት ወደማፍራት መሸጋገራቸውን ይናገራሉ፡፡
በበርካታ ማህበራት ዘንድ የሚስትዋለው ያለመተባበርና በአብሮነት ያለመዝለቅ ችግር ለውጤታማነት መጥፋት እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ እነኚህ ወጣቶች ግን ስራዎቻቸውን በፍቅርና በመተባበር እንደሚሰሩና ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንዲችሉ ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
የወረዳው ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽ/ቤት የእንስሳት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ተረፈ በቀለ ለንብ እርባታ ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ ለተሰማሩትም የክህሎት ስልጠናና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ ጫካ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/