በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ሙላት በሰዉ፣ በእንስሳትና በንብረት ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አከባቢ ልማት ቢሮ ገለጸ

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ሙላት በሰዉ፣ በእንስሳትና በንብረት ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አከባቢ ልማት ቢሮ ገለጸ

የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የኦሞ ወንዝን በዘመናዊ መስኖ ተጠቅሞ በማልማት የምግብ ዋስትናውን ያረጋግጥበት የነበረው የዘመናት ባለውለታው ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ወንዙ በተደጋጋሚ በመሙላት በዳሰነች ወረዳ በሰዉ በእንስሳትና በንብረት ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አከባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ሀብቴ ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮዉ የውሃ ሙላት ከወትሮው እጅግ በጣም የተለየ ነው ያሉት ኃላፊዉ በ33 ቀበሌያት 3000 ሄክታር በዘር የተሸፈነ የእርሻ መሬት እና 86 ሺ ሄክታር የግጦሽ መሬት እንዲሁም ለመስኖ ተቋማት አገልግሎት የሚውሉ የውሃ ማቀበያ ፓምፖችን ጨምሮ በርካታ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በውሃው በመዋጣቸዉ ከ62 ሺ በላይ የሚሆኑ አርብቶ አደሮችን እና 2.3 ሚሊየን የሚጠጉ እንስሳትን ከመኖሪያ ቀያቸው በማፈናቀሉ አርብቶ አደሩን ለከፋ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ማጋለጡን ገልጸዋል፡፡

ይህንን ማህበረሰብ ለመታደግም እየተሰሩ ካሉ ስራዎች ባሻገር ሁሉም አካላት ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

የደቡብ ኦሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ጋርሾ በበኩላቸው የኦሞ ወንዝ ለተከታታይ 5 ዓመታት እየሞላ በዳሰነች አርብቶ አደሮች ላይ ጉዳት እያስከተለ የቆየ ቢሆንም ተፈናቃይ አርብቶ አደሮች በሚፈለገው ደረጃ ድጋፍ እያገኙ እንዳለሆነ ጠቁመዋል፡፡

ጉዳዩ አሳሳቢ ስለሆነ የእለት ጉርስ ከማቀረብ አንስቶ ሌሎች ድጋፎችን እንዲሁም ደሴት አከባቢ የሚኖሩ አርብቶ አደሮችን ለማውጣት ወረዳዉ ላይ ያለው 1 ጀልባ ብቻ በመሆኑ የወረዳዉን አርብቶ አደር ለመታደግ ሁሉም አካላት ድጋፍና እገዛ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡

የአርብቶ አደር አከባቢ የመስኖ ተቋማት ጥገና፣ አጠቃቀምና አስተዳደር ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፈለቀ ስዩም እና የመስኖ መሐንዲስ አቶ ያዘው አፈወርቅ በጋራ እንደገለጹት ይህ የውሃ ሙላት የአርብቶ አደሩን ህይወት በምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለመቀየር በወንዙ ዳርቻ የሚገኙ 28 ቀበሌያትን የሚያለሙ ትላልቅ የመሰኖ ልማት ተቋማት ላይ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞርቴ ተፖስ የወንዙ ሙላት ከዚህ ቀደም ከነበሩ ተፈናቃዮች ባሻገር ወደ 17 ሺ የሚጠጉ አዳዲስ አርብቶ አደሮችን በማፈናቀሉ የተፈናቃዮች ቁጥር በመጨመሩ የተነሳ ከዚህ ቀደም ከነበሩ በ11 የመኖርያ ማዕከላት ወደ 13 ከፍ ማለቱን ገልጸው ወንዙ በሰዉ፣ በእንስሳትና በንብረት ላይ የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመታደግ ሁሉም በጋራ እንዲደግፍና እንዲያግዝ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡

ከተፈናቃዮች መካከል ኧረግ ዾኮል እና ቡይቴ ኜይቴ የኦሞ ወንዝ ለተደጋጋሚ አመታት ጉዳት እንዳደረሰባቸዉ ተናግረው አሁን ንብረታቸዉን ትተዉ ልጆቻቸዉን ብቻ ይዘው የወጡ ቢሆንም ምንም ዓይነት የምግብም ሆነ የመገልገያ ቁሳቁስ ስለሌላቸዉ በችግር ውስጥ መሆናቸዉን ገልፀው እርዳታ እንዲደረግላቸዉ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን