አካባቢዉ በቁም እንስሳት ሀብት እምቅ አቅም ቢኖረውም ህጋዊ የግብይት ማዕከል ባለመዘጋጀቱ ምክንያት ከዘርፉ ወረዳዉም ሆነ አቅራቢ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ አለመሆናቸውን በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ የይና ቀበሌ ነዋሪዎች ተናገሩ

አካባቢዉ በቁም እንስሳት ሀብት እምቅ አቅም ቢኖረውም ህጋዊ የግብይት ማዕከል ባለመዘጋጀቱ ምክንያት ከዘርፉ ወረዳዉም ሆነ አቅራቢ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ አለመሆናቸውን በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ የይና ቀበሌ ነዋሪዎች ተናገሩ

የወረዳዉ ገቢዎች ጽህፈት ቤት በበኩሉ ህገወጥ ግብይትን ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቱን ገልጿል።

በህገወጥ መንገድ የቁም እንስሳት ላይ ግብይት የሚፈጽሙ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግ የቁም እንስሳት አዋጅ ቁጥር 819/2006 የጸደቀ ቢሆንም ተከታትሎ ከማስፈጸም አንጻር ዉስንነቶች ይስተዋላሉ ተብሏል።

በማሻ ወረዳ ይና ቀበሌ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ዘዉደ ገበየሁና አቶ ገቦ ዳሾ በሰጡት አስተያየት በቀበሌያቸዉ በአንድ ግለሰብ በነፍስ ወከፍ 20 እና ከዚያም በላይ ሰንጋዎችን የማደለብ ልምድ ቢኖርም ህጋዊ የግብይት ማዕከል ተቋቁሞ ተገቢውን አገልግሎት ባለመስጠቱ ምክንያት እንደ ልፋታቸዉ ተጠቃሚ አለመሆናቸዉን ገልጸዋል።

በህገ ወጥ ግብይት ምክንያት ወረዳዉ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባዉን ገቢ ከማጣቱ ባሻገር በየጊዜው በርካታ ቁጥር ያለቸዉ ሰንጋዎች ከወረዳዉ በህገ ወጥ መንገድ ወጥተዉ በሌሎች ወረዳዎች ስም በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ለገበያ ቀርበዉ በተሻለ ዋጋ እንደሚሸጡም አርሶ አደሮቹ አክለዋል።

የሚመለከታቸዉ አካላት ለችግሩ አፋጣኝ መፍተሔ እንዲፈልጉም ጠይቀዋል።

የማሻ ወረዳ ገቢዎች ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ኪዳነ በበኩላቸዉ ወረዳዉ በቁም እንስሳት ሀብት እምቅ አቅም ያለውና አመቱን ሙሉ ሰፊ አቅርቦት ያለዉ መሆኑን በመረዳት በወረዳዉ ሶስት የቁም እንስሳት የግብይት ማዕከሎች ቢያቋቁምም ህገ ወጦችን ከመቆጣጠር አንጻር ሰፊ ችግሮች መስተዋላቸዉን ነዉ የተናገሩት።

የቁም እንስሳት ግብይት ጋር ተያይዞ ለአቅራቢዎችና ለነጋዴዉ ማህበረሰብ በተለያዩ ጊዜ መድረኮችን በማዘጋጀት ግንዛቤን ሲያስጨብጡ መቆየታቸዉንም አክለዋል።

አሁን ላይ ህገወጥ የእንስሳት ግብይትን ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባታቸዉንም ጭምር አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል።

የቁም እንስሳትን ለመቆጣጠር የጸደቀዉን አዋጅና መመሪያዎችን የጣሰ ማንኛዉም አካል እንስሳቱን ከማስወረስ ባለፈ በእስራትና በገንዘብ እንደሚያስቀጣ በማወቅ ህጋዊ አሰራሮችን መከተል እንደሚገባዉ አሳስበዋል።

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ህገወጥነትን በመከላከልና መረጃዎችን ለሚመለከታቸው አካላት በማድረስ የተለመደዉን ትብብር እንዲያጠናክሩ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሀላፊ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ ታሪኩ ታደሰ – ከማሻ ጣቢያችን