በሆሳዕና ከተማ ከነባሩ አስፋልት መንገዶች 5.65 ኪሎ ሜትር ደረጃ የማሻሻል ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ
ይህ የተገለጸው የከተማው የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አማካሪ ምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት ነው።
በሆሳዕና ከተማ በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ 60 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ለመገንባት ታቅዶ የተጀመረው የ14 ነጥብ 134 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ግንባታ በመጪው የካቲት ወር ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
ከዚህ ጎን ለጎንም በመሃል ከተማ ከአገልግሎት ውጭ ከሆኑ 10 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ነባር አስፋልት መንገድ 5 ነጥብ 65 ኪሎ ሜትሩን ደረጃ የማሻሻል ስራ እየተከነወነ እንደሚገኝ የፕሮጀክቱ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ደመቀ ኃይሌ ገልፀዋል።
የግንባታ ስራው ደንብና መመሪያን በተከተለ መልኩ አስፈላጊውን ሂደት አልፎ ግንባታ ስለመጀመሩም በዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በሆኑት አቶ አብርሃም መጫ በኩልም ተጨማሪ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በ14 ነጥብ 134 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ግንባታ ሂደት የተስተዋለው የመንገድና የፍሳሽ ማስወገጃ አለመጣጣም በነባሩ አስፋልት ማሻሸያ ግንባታ እንዳይደገም በ4 መቶ 95 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ ሁለቱም ሳይነጣጠሉ በአንድ ተቋራጭ እንደሚገነቡ ስለመደረጉም ተጠቅሷል።
ያነጋገርናቸው የጠቅላላው ጉባኤ ተሳታፊዎችም ለፕሮጀክቶቹ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ የገለፁ ሲሆን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ሰለሞን የከተማውን ገቢ በቅንጅት መሰብሰብ ከተቻለ ከመንገዶቹ ባለፈ በበጀት ዓመቱ የተያዙ ሌሎች ፕሮጀክቶችንም ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በራስ አቅም የሚገነቡ እንደመሆናቸው በአፈፃፀም ወቅት በግንባታ ጥራት፣ በበጀትና በሌሎችም ጉዳዮች የሃሳብ ድጋፍ በማድረግ ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣም ተጠይቋል።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በጋራ ተባብረን የህዳሴ ግድብን እንዳሳካን የማህበረሰባችን የጤና ችግሮችን በተለይም እናቶችንና ህጻናትን በዘላቂነት ከወባ በሽታ መታደግ እንችላለን – ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ/ር)
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት ለወደባችን ጉዞ ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው ሲሉ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ
የካፈቾ ዘመን መለወጫ “ማሽቃሮ” በቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተከበረ