የቡሌ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት የትምህርት ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስታወቀ

የቡሌ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት የትምህርት ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስታወቀ

ደብሪቱ በየነ እና ዘካሪያስ ደምሴ የቡሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛና 10ኛ ክፍል ተማሪዎች እያሽቆለቆለ የመጣውን ውጤት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት በየትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ የግብአት ችግሮች ፈተና መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቡሌ ከተማ ሠፈረ ሠላም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጌዴኡፋ ትምህት መምህር ዮሴፍ ታምሩ የትምህርት ሥራ በወቅቱ መጀመሩን ገልጸው ከአጀማመሩ አስቀድሞ ምቹ የመማሪያ ስፍራ ለመፍጠር በርካታ ተግባራት መከወናቸውን ተናግረዋል።

የባሪቻ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና ርዕስ መምህር ዮሴፍ ታምራት በበኩሉ የመጽሐፍት ችግር ለመቅረፍ ሶፍት ኮፒ ለመምህራን በማዳረስ ተማሪዎችም ቤተ መጽሐፍት እንዲጠቀሙ በኮፒ እያቀረቡ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የቡሌ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ያሲን እነደገለጹት “ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ንቅናቄ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተጨማሪ አዳዲስ ክፍሎች ማስፋፊያና ጥገና ሥራ፣ የመምህራን ማደሪያና መናፈሻዎች የማደራጀት ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

ህብረተሰቡ በዓይነት፣ በጉልበትና በገንዘብ ባደረገው ድጋፍ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ተሰብስቦ በትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት የማሟላት ሥራ እየተከናወነ ነው ያብለዋል፡፡

ከመማሪያ መጽሐፍት ጋር ተያይዞ ከወረዳው አስተዳደር በተገኘው ገንዘብ በጊዜያዊነት ችግሮችን ለመቅረፍ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በቤተመጽሐፍት እንዲጠቀሙ እና ለአደንኛ ደረጃ ተማሪዎች በየምዕራፎቹ ፎቶ ኮኘ በማድረግ የማዳረስ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ እየተሠራ ባለው ተግባር ሁሉም ባለድርሻዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው- ከፍስሀገነት ጣቢያችን