የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤቶችን ምቹ የመማር ማስተማሪያ ስፍራ በማድረግ

የትምህርት ጥራት ለማምጣት እያደረገች ያለውን ጥረት አጠናክራ እንድትቀጥል የሀዲያ ዞን ትምህርት መምሪያ ጠየቀ

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ የከፑችን ታናናሽ ወንድሞች ማሕበር በሆሳዕና መድኃኒአለም ትምህርት ቤት ያስገነባውን ባለ ሁለት ወለል ሕንፃ አስመርቋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሀዲያ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ ዶ/ር ክበሞ ዴታሞ ያደጉ ሀገራት ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ቢያስፋፉም የዕድሜውን ያህል ሳያድግ መቆየቱን አንስተዋል።

በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ከጥራት ይልቅ መጠነ ማለፍ ላይ ትኩረት መደረጉ በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደቻለ ያስረዱት ዶ/ር ክበሞ መንግስት በትምህርት ዙሪያ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከጀመረ ወዲህ የትምህርቱ ማሕበረሰብ መነቃቃት መጀመሩን ተናግረዋል።

በዞኑ ካሉ 600 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 86 በመቶዎቹ ከደረጃ በታች መሆናቸውን የገለጹት ሀላፊው መንግስት ደረጃውን በማሻሻል የትምህርት ጥራት ለማምጣት መሠረተ ልማትና ግብዓት የማሟላት ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በዞኑ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የመንግስትን ዓላማ ከመደገፍ ባለፈ በየደረጃው የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ለሌሎች አርአያ እየሆነ እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር ክበሞ ተግባሩን በገጠር አካባቢ እንዲያስፋፋ ጠይቀዋል።

በቤተክርስቲያኑ የኢትዮጵያ የከፑችን ታናናሽ ወንድሞች ማህበር የበላይ ሀላፊ ዶ/ር አባ ገብረወልድ ገ/ጻድቅ የሰው ልጅ ያለ ልዩነት የሚገለገልበትን የልህቀት ማዕከል በጥራት ገንብቶ መስጠት የማሕበሩ ግብ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዕለቱ በ23.2 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ለምርቃት የበቃው የሆሳዕና መድኃኒአለም ትምህርት ቤት ሕንፃ የዚሁ አካል እንደሆነ የጠቆሙት ሀላፊው ተግባሩን የበለጠ የማስፋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የሆሳዕና ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነስዩም ፍራንሷ በበኩላቸው ህንጻውን የገነቡትን ለጋሽ አካላት አመስግነው ቤተክርስቲያኗ ከመንፈሳዊ ስራ ጎን ለጎን በንጹሕ መጠጥ ውሃ፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፍ ያለቀለምና ሃይማኖት ልዩነት እየሰራች ያለውን ተግባር አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

በዕለቱ የተገኙ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ልጆቻቸው ደረጃውን በጠበቀ ትምህርት ቤት እንዲማሩ ምቹ ሁኔታ የፈጠረውን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አመሰግነው ተማሪዎች የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የድርሻቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዕለቱም በ2015 የትምህርት ዘመን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ላጠናቀቁ ተማሪዎች የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ሲሆን ለ3ኛ ምዕራፍ የሕንፃ ግንባታም የመሠረት ድንጋይ የማኖር ስነስርዓት ተካሂዷል።

ዘጋቢ: ጌታቸው መጮሮ – ከሆሳዕና ጣቢያችን