“እግዚአብሄርን መፍራት እና ትምህርት መውደድን ከእናቴ ወርሻለሁ” – ዶ/ር ፌቨን አማረ
በኢያሱ ታዴዎስ
እናት በሆዷ ውስጥ ያለውን ጽንስ ስትንከባከብ ቆይታ ፍሬዋን ልታይ ተቃርባለች። ፍሬዋ ደግሞ በኩር በመሆኑ ክትትሏ ልዩ ነበር። ጽንሱ በቀናት ውስጥ እንደሚወለድ አልተጠራጠረችም። ቀኑ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የመውለድ ጉጉቷም እንዲሁ ጨመረ። አንዲት ምሽት የእናትን ምኞት ልታሳካ ከተፍ አለች። እናት ጽኑ ምጥ ይዟት ሆሳዕና ንግስት እሌኒ ሆስፒታል ገብታለች።
ከወዲያ ደግሞ አባት የምስራች ለመስማት ቋምጦ በሆስፒታሉ ኮሪደሮች ጎርደድ ጎርደድ ይላል። የማይደርስ የለምና ውድቅት ሌሊት ላይ አንዲት እንግዳ ልጅ ይህን ዓለም ተቀላቀለች። ይህ ለቤተሰቡ ትልቅ ደስታ ነበር። ግንቦት 17 ማክሰኞ ዕለት 1986 ዓ.ም ህጻን ፌቨን አማረ ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ስጦታ ተደርጋ ከአምላክ ዘንድ ተቸረች። ታዲያ ይህቺ ህጻን በኩርነቷ ከማህጸን ጀምሮ እንክብካቤ ሳይለያት እንድታድግ አደረጋት። በስስት የሚያዩዋት እናትና አባቷ እንደ ህጻን ልጅ ማግኘት ያለባትን ፍቅር ሁሉ ሰጧት። እሷም ቀስ በቀስ እየዳኸች፣ ራሷን ችላ ለመራመድ በቃች።
ሁለት ዓመት ሲሞላት ደግሞ ወላጆቿ እህት በስጦታነት አበረከቱላት። ህጻን ሎዛ አማረ ተከተለች። አንድ ከመሆን ሁለት ወደ መሆን። ይህም ለቤተሰቧ ሌላ ደስታ አመጣ። ፌቨን ሶስት ዓመት ሲሞላት የቤተሰቧ ደስታ ላይ ውሃ የሚቸልስ አጋጣሚ ተከሰተ። አባቷን በሞት ተነጠቀች። ይሄኔ እሷም ሆነች ታናሽ እህቷ ነፍስ ስለማያውቁ ህመሙን አልተረዱትም ነበር። ሙሉ የቤተሰቡ ሸክም ግን እናት ጫንቃ ላይ አረፈ። እናትም ብርቱ ነበረችና ሁለቱን ልጆቿን ለማሳደግ አልሰነፈችም። በጎን በቤተክርስቲያን መሪነት መንፈሳዊ አገልግሎት እያገለገለች ሁሉን ለአምላኳ ሰጥታ በጽናት ልጆቿን ማሳደግ ጀመረች።
ፌቨንና ሎዛም እንደ ልጅ ቦርቀው የወዳጅ ዘመድ ፍቅር ሳይጎድልባቸው የልጅነት ጊዜያቸው ሰመረ። ፌቨን ለአቅመ ትምህርት ስትደርስ በወቅቱ ሆሳዕና መዋዕለ ህጻናት የተሰኘው (አሁን ቪዥን አካዳሚ ተሰኝቷል) የግል ትምህርት ቤት ተቀላቀለች። ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስም በዚያው ተማረች። ታዲያ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ብዙ ነገር ከእናቷ ተምራለች። ፍቅር፣ ቆራጥነት፣ እግዚአብሄርን መውደድ፣ ሌላው ቢቀር ኃላፊነትን መሸከምን ከእናቷ ወርሳለች። እናቷ ልጆቿ ኃላፊነትን እንዲማሩ ስራ ከፋፍላ ትሰጣቸው ነበር።
ለቤት የሚያስፈልጉ እንደ አስቤዛ ያሉ ግብዓቶችን ዝርዝራቸውንና ዋጋቸውን ከማወቅ ጀምሮ ሄዶ ሸምቶ ጥቅም ላይ ማዋል የፌቨን ድርሻ ነበር። በዚህም እሷና እህቷ ሎዛ በትንሽ በትንሹ ኃላፊነትን ለመዱ። ፌቨን ሰባተኛ ክፍል ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች በህመም ምክንያት እናቷን በሞት ተነጠቀች። ይህ ለእሷና ለታናሽ እህቷ መሪር ሃዘን ነበር። ሰማይ የመደፋት ያህል። ሃዘኑ በቀላሉ ሊለቃቸው አልቻለም። ገና በታዳጊነታቸው ወላጆቻቸውን አጥተው ኑሮን የመጋፈጥ ፈተና ተደቀነባቸው።
የዚህን ጊዜ ግን አይዟችሁ ባይ ወገን አልጠፋም። የክርስትና እናቷ (እርሷ እቴቴ ብላ የምትጠራቸው) እንዲሁም ቄስ ፍቅረኢየሱስ የተባሉ መንፈሳዊ አባቷ ከዘመዶቻቸው ጋር ከነበሩበት ሃዘን ወጥተው እንዲጠነክሩ ከጎናቸው ሆነው ይመክሯቸው እንደነበር ፌቨን ታስታውሳለች። “ከሁሉም ግን ከዚያ መሪር ሃዘን በእግዚአብሄር እርዳታ ነው የወጣነው” ስትልም ፈጣሪዋን ታመሰግናለች። መቼም ህይወት መቀጠሏ አይቀርምና ወላጆቻቸውን ካጡ በኋላ ለብቻቸው ለመኖር ዕድሜያቸው እንደማይፈቅድ ዘመድ ወዳጆቻቸው በመምከር ወደ ቡታጅራ አክስታቸው ዘንድ ሄደው እንዲማሩ ተወሰነ። ቀጣይ መዳረሻቸውም ቡታጅራ አክስታቸው ጋር ሆነ።
ወደ ቡታጀራ ሲዛወሩ ሁሉም ነገር አዲስ ሆነባቸው። ከተማዋ፣ ማህበረሰቡ፣ ትምህርት ቤቱ። እስከሚለማመዱ ድረስም ጥቂት ጊዜ ወሰደባቸው። ፌቨንም 8ኛ ክፍል ትምህርቷን በቡታጅራ ጁኒየር ትምህርት ቤት ቀጠለች። 9ኛ እና 10ኛ ክፍል ትምህርቷንም በቡታጅራ መቂቾ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራ አጠናቀቀች። የ10ኛ ክፍል ማትሪክ ውጤቷም 3 ነጥብ 6 ነበር። አጠቃላይ የቡታጅራ ከተማ ቆይታቸው ከሶስት ዓመታት አልዘለለም። ወደ ሆሳዕና ከተማ ተመለሱ። ይህን ጊዜ ግን ኑሯቸውን ለብቻቸው ለመምራት ተገደዱ።
ከወላጆቻቸው በወረሱት ቤት እየኖሩ፣ እንዲሁም ግቢያቸው የሚገኘውን ሰርቪስ ለመንግስት ቢሮነት በማከራየት ራሳቸውን ያስተዳድሩ ጀመር። ያኔ እናቷ ያስተማረቻቸው ኃላፊነት የመሸከም አቅም በዚህ ጊዜ መገለጥ ጀመረ። ፌቨን ትምህርቷን ቀጥላ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል በሆሳዕና ቪዥን አካዳሚ ተምራ አጠናቀቀች። የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስዳ 502 ነጥብ ነበር ያመጣችው። ይህም በወቅቱ ከፍተኛ ነበር። ትምህርቷን እንድትወድ ያደረገቻት እናቷ እንደሆነች ትናገራለች:- “እናቴ ያወረሰችኝ እግዚአብሄርን መፍራት እና ትምህርት መውደድን ነው። እግዚአብሄር በብዙ አግዞኛል። በዚህም ምክንያት በትምህርቴ ጎበዝ ነበርኩ።
ከዚህ በዘለለ የገጠመኝ ችግር በራሱ ጎበዝ ተማሪ እንድሆን አድርጎኛል። ችግሬን ለመጋፈጥ ስል የተማርኩት ትምህርት ውጤታማ ለመሆኔ ምክንያት ነበር።” ፌቨን ቀጣይ መዳረሻዋ ያደረገችው ሀዋሳ ከተማ ነበር። በ2006 ዓ.ም የመጀመሪያ ምርጫዋ የነበረው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና የህክምና ትምህርት ሰምሮላት ለመማር ተሰናዳች። ይሁን እንጂ የዩኒቨርሲቲ ህይወቷ ከጅምሩ ቀላል አልሆነላትም። በአንድ በኩል ታናሽ እህቷን ለብቻዋ ትቶ መማሩ ተራራ የመግፋት ያህል ከበዳት። በሌላ በኩል በዩኒቨርሲቲው አዲስ ከባቢ መልመዱ አዳጋች ሆነባት።
በዚህም ምክንያት ወደ ሆሳዕና ለመዛወር አስባ ነበር። ነገር ግን የእህቷ ጠንካራ መሆን ብርታት ሰጣትና ትምህርቷን በዚያው ቀጠለች። ትምህርቷም ቢሆን ቀላል አልሆነላትም። እንደ ባህር የገዘፈው የህክምና ትምህርት ብዙ ጥረት የሚጠይቅ ሆኖ አገኘችው። የቤተሰቧን ሸክም በጫንቃዋ ተሸክማ እሱን ለማስተካከል ላይ ታች ማለቷ አልቀረም። በጎን ደግሞ በትምህርቷ ውጤታማ ለመሆን ትግል ማድረጓ ትልቅ ጫና ፈጠረባት። የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ሳለችም እህቷ ሎዛ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ደርሷት ለሁለት ቤት ተከራይተው መማር ጀመሩ።
በዚህ ወቅት ፌቨን ላይ የነበረው ጫና በተወሰነ ደረጃ ቀንሷል። በብዙ ትግልም የፈጣሪ እገዛ ታክሎ የህክምና ትምህርቷን በስድስት ዓመት ከመንፈቅ ለማጠናቀቅ በቃች። “ለዚህ ስኬቴ ከጎኔ ሆነው ላበረቱኝ ጓደኞቼና ሀዋሳ የሚገኙት ዘመዶቼን በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግን አላልፍም” ትላለች። ከዚያ በኃላ ፌቨን ዶክተርነቱን ከነሙሉ ማዕረጉ ተጎናጸፈች። እኛም ቀጣይ የህይወት ተረኳን በዶክተርነት ማዕረጓ ለመተረክ ተገድደናል። ዶ/ር ፌቨን አማረ ከዩኒቨርሲቲ ቆይታ በኋላ ለአራት ወራት ያለስራ ካሳለፈች ወዲህ በሀዲያ ዞን ጊንቢቹ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በጠቅላላ ሀኪምነት ስራ ጀመረች።
የስራ ባልደረቦቿና የአካባቢው ማህበረሰብ ፍቅር ስለለገሳት በስራዋ ደስተኛ ነበረች። በሆስፒታሉ የነበራት ቆይታ ግን ከአንድ ዓመት አልዘለለም። በጊንቢቹ ሳለች ሁለተኛ ድግሪዋን በጀነራል ፐብሊክ ኸልዝ የትምህርት ክፍል መማር ጀምራ ነበር። አሁን በቀጣዩ ጥቅምት ወር ሁለተኛ ድግሪዋን ታጠናቅቃለች። ከጊንቢቹ መልስ ወደ ሆሳዕና ተዛውራ በቦቢቾ ጤና ጣቢያ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ ሰራች። በቦቢቾ ጤና ጣቢያ ስትሰራ፣ ጎን ለጎን ከእህቷ ጋር በመሆን “አቤንኤዘር የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ጅምላ አከፋፋይ” የሚል ሱቅ ከፈተች።
የሱቃቸውን ስያሜ “አቤንኤዘር” ያሉበትም የራሱ ምክንያት አለው። አባቷ አቶ አማረ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፋርማሲስትነት ከተመረቀ በኋላ በሆሳዕና ከተማ የከፈተውንና በከተማዋ የመጀመሪያ የሆነውን አቤንኤዘር የመድኃኒት መሸጫ መደብር በመታሰቢያነት ለማሰብ ነበር። ከጊዜ በኋላም የጤና ጣቢያ ስራውን ትታ ፊቷን ሙሉ ለሙሉ ወደ ሱቁ አዞረች። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ “ያማረ ፋርማ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር” የሚል የመድኃኒትና ህክምና መሳሪያዎች አምጪና ላኪ ድርጅት ከእህቷ ጋር ከፍተው በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ። እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ጎጆ ለመቀለስም መንገድ ጀምራለች።
ታዲያ ያንን ሁሉ በፈተና የታጀበ ህይወት ያለፈችበትን መንገድ ዛሬ ላይ ሆና ስታስበው:- “እግዚአብሄር በሁሉ ረድቶኛል። ያለፍኩበት መንገድ ጥንካሬ ሆኖኛል። ያሳለፍኳቸው አስቸጋሪ ጊዜያት ሁሉ አስተምረውኝ አልፈዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ሲሆን ብዙ እንደሚሆን ተምሬያለሁ። እናቴም በሕይወቴ ትልቅ አሻራ አሳርፋ አልፋለች። ያኔ በልጅነት አዕምሯችን ስትመክረን የነበረው ምክር ለህይወት ዘመን ሆኖልኛል።” ትላለች። የ
ዶክተር ፌቨን ህይወት እንደሰመረ ቀጥሏል። ትናንት ትግል የበዛባቸው ፈተናዎቿ ዛሬ ላይ የስኬት ፍሬን እንድትበላ አድርገዋታል። የሰው ልጅ ህይወቱ እስካለች ድረስ ተስፋ እንዳለው ማሳያ የመሆኗ ምስጢርም እነዚህ ፈተናዎቿ ናቸው።
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ