“ልመናን ለመሰለ አሳፋሪ ተግባር እጅ አልሰጠሁም” – ወታደር መለቆ ቴማ
በደረሰ አስፋው
ከዝናብ ለመጠለል ድንገት ወደ መንደራቸው ጠጋ ባልኩበት ጊዜ ነው ያገኘኋቸው፡፡ የተወለዱበትን ጊዜ በውል ለመናገር ቢያዳግታቸውም ከቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ዘመነ-መንግስት በፊት ነው አሉኝ። በዚህ ስሌት ከ80ዎቹ ዕድሜ የተሻገሩ እንደሆነም ገመትኩ፡፡
ከቤታቸው በር ለስራ ባዘጋጇት አነስተኛ መደብ ላይ ተቀምጠው ይሰራሉ፡፡ በግራና ቀኝ ታስረው ቅጠላቅጠል የሚመገቡ ፍየሎች አሉ፡፡ ለሽያጭ የተዘጋጁ ቁሳቁሶችም በአይነት በአይነታቸው ተሰቅለዋል፡፡ ለሚያመርቷቸው ምርቶች በጥሬ እቃነት የሚጠቀሙባቸው ዕቃዎችም እንዲሁ ስፍራውን ይዟል፡፡ ሰው ለማናገር እንኳ ጊዜ ያላቸው አይመስሉም፡፡ አልፎ አልፎ አይናቸውን ጣል ከሚያደርጉባቸው ፍየሎች በስተቀር ጊዜያቸውን በሌላ ጉዳይ አያባክኑም። የጎረቤት ሰዎች መጥተው ሲያናግሯቸው ትዕዛዝ አለብኝ ነው መልሳቸው። ቅልጥፍናቸው አግራሞትን ይፈጥራል፡፡
ሰላምታ ተለዋውጠን ላናግራቸው እንደምፈልግ ቀጠሮ ይዘን ተለያየን። በቀጠሯችን ቀንም ተገናኘን፣ ተዋወቅን፡- ወታደር መለቆ ቴማ ወቢሎ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት በወላይታ ዞን ኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ነው፡፡ ከአርሶ አደር ማህበረሰብ የተገኙት ወታደር መለቆ ወቅቱ የትምህርት ዕድል ለማግኘት አዳጋች ቢሆንም እሳቸው ግን እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ ከስድስተኛ ክፍል በኋላ ግን ትምህርታቸውንም ሆነ መኖሪያቸውን ትተው ወደ ሀዋሳ መጡ፡፡ የአሁኑ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ግብርና ካምፓስ በቀድሞ ሀዋሳ ግብርና ኮሌጅ በአትክልተኛነት ተቀጥረው መስራት ጀመሩ፡፡
የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት ከስልጣኑ ተወግዶ ደርግ ስልጣኑን ሲይዝ የሳቸውም የስራ አድራሻ ተቀየረ፡፡ የደርግ መንግስትን የእናት ሀገር ጥሪ ተቀብለው በፈቃደኝነት ለውትድርና ተመዘገቡ፡፡ በ1970 ዓ.ም መጀመሪያ በታጠቅ ጦር ሰፍር የሚሰጠውን ወታደራዊ ስልጠና ለሶስት ወር ተከታተሉ። በድጋሚ በሁርሶ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የሚሰጠውን ስልጠና ለ6 ወር ወሰዱ፡፡ ከስልጠናው በኋላ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት በተራራው ክፍለ ጦር በትግራይ ግንባር ውጊያ ላይ ተሳታፊ ሆኑ፡፡
በኤርትራ ከረን ግምባርም ተሰልፈው ከጠላት ጋር ተፋልመዋል፡፡ በዚሁ ግንባር በ1975 ዓ.ም አንድ እግራቸውን ተመተው ለጉዳት ተጋለጡ፡፡ በአስመራ ገጀረት ሆስፒታል የመጀመሪያ ህክምናቸውን አገኙ፡ ፡ ጉዳቱ የጠና ሆነና ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መጥተው ህክምናቸውን ተከታተሉ፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቢቆዩም ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ ወደ ስራ አልተመለሱም። ጡረታ ወጡ፡፡ ለአካል ጉዳቱም ምክንያት የሆነው ይሄው በአንድ እግራቸው ላይ የደረሰባቸው ጉዳት ነበር፡፡ ከጡረታ በኋላ ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሀዋሳ በመምጣት መኖር ጀመሩ፡፡ ከጉዳቱ ጋር ሆነው ህይወታቸውን መምራት ግድ አላቸው፡፡ የቀን ስራን እያፈላለጉ በመስራት ህይወታቸውን ቀና ለማድረግ ጥረት ማድረግ ጀመሩ፡፡
ችግሩ ግን በዛ፡፡ የአካል ጉዳት ሲደመር ስራ ማጣት፡፡ ያም ሆኖ ቤት የሚገነባባቸውን ቦታዎች እያሰሱ ከአናጺዎች ጋር በረዳትነት ተቀጥረው መስራት ጀመሩ፡፡ በሂደትም ሙያቸው አድጎ እራሳቸውን ችለው መስራት ጀመሩ፡፡ በእግራቸው ላይ ያለው ጉዳት ፈጽሞ መዳን ባለመቻሉ እየጠዘጠዘ የስራቸው እንቅፋት ሆነ፡፡ የግለሰብ ድርጅት ውስጥ በጥበቃ ተቀጥሮ መስራትን የህመማቸው ማስታገሻ አደረጉት፡፡ ህመማቸው ታገስ ሲልላቸው ግን ተቀምጦ ከመዋል ተንቀሳቅሶ መስራትን መረጡ፡፡ የአህያ ጋሪ ገዝተው በከተማው ውስጥ ለግንባታ የሚያስፈልግ ውሃ በመሸጥ ስራ ተሰማሩ፡፡ “መቀመጥ ለኔ በሽታ ነው” የሚሉት ወታደር መለቆ ውሃውን እያዞሩ በመሸጥ በርካታ ደንበኞችን አፈሩ፡፡ የገቢ አቅማቸው አደገ፡፡ የአካል ጉዳታቸውን ላለመስራት ምክንያት አያደርጉም ነበር፡፡ በዚህ ላይ እያሉ ግን ሌላ እክል አጋጠማቸው፡፡
ኮረም ሰፈር ይኖሩበት የነበረው የቀበሌ ቤት ለልማት በሚል እንዲፈርስ ተደረገ፡፡ አካባቢውን ለቀው በምትክ ወደተሰጣቸው ጨፌ አካባቢ ገቡ። ለሰፈሩ ግን እንግዳ ሆኑ፡፡ እንደቀድሞ ውሃ በጋሪ እያዞሩ መሸጥ አዳጋች ሆነባቸው። “እጆቼ ስራ ፈተው መዋል ማደር አይሹም” የሚሉት ወታደር መለቆ ሌላ የስራ አማራጭን ማየት ጀመሩ፡፡ ከሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚወገዱ ተረፈ ምርቶችን ተመለከቱ፡፡ ለዚህም መላ ሊያበጁለት አሰቡ፡፡ ተረፈ ምርቱን በመኪና ጭነው የሚያስወግዱ ሰዎችን ምርቱን እንዲሸጡላቸው ተስማሙ፡፡ በተጨማሪም በከተማ የሚጣሉትንም ዞረው በመልቀም ምርቱን በስፋት አከማቹ፡፡ በቂ ግብአት ማዘጋጀታቸውን ሲረዱ ከመኖሪያ ቤታቸው ጎን የመስሪያ ቦታ አዘጋጁ፡፡ ይህ ቦታ ዛሬ ላይ ዘንቢል፣ ገመድ፣ ስጋጃ ማርገብገቢያና ጭራዎችን በመስራት ለሽያጭ የሚያቀርቡበት ሆኗል፡፡
የሚጣለውን መልሶ በማልማትም አካባቢው እንዳይበከል አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ያነሳሉ፡፡ ስራ መፍጠራቸውም ከችግር እንደታደጋቸውም እንዲሁ ተናግረዋል፡፡ ዛሬ ሰርቶ በመሸጥ የገቢ ምንጭ ፈጥረዋል፡፡ የሚሰሩትን ስራ በእጅ ጋሪ አዙረው ይሸጣሉ፡፡ የገጠማቸው የገበያ ችግር እንደሌለም ገልጸውልኛል፡፡ ደንበኞችንም አፍርተዋል፡፡ በሽምግልና ጊዜያቸው ሰርተው እራሳቸውን በመቻላቸው የሚያበረታቷቸው እንዳሉም ነግረውኛል፡፡ አካል ጉዳተኛው ወታደር መለቆ ከዚህ ስራቸው ጎንም ሌላ ስራ አላቸው፡፡ በቁጥር አነስተኛ ቢሆንም ፍየሎችን ያረባሉ። በዘመን መለወጫ በዓልም ካረቧቸው ሙክቶች ሸጠው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸውልኛል፡፡ በቤት ውስጥ ዶሮዎችንም በማርባት ከፍጆታ የተረፈውን እንቁላል ለሽያጭ ያውላሉ፡፡ ባለቤታቸው በሞት ሲለዩ የቤተሰቡ ኃላፊነት የወደቀው በእሳቸው ነው፡፡ ሁለት የራሳቸው ልጆችንና ሌሎች የልጅ ልጆችን ያሳድጋሉ፡፡ “ጉልበቴ ቢደክምም እጅ አልሰጠሁም” የሚሉት ወታደር መለቆ “መለመንን ለመሰለ አሳፋሪ ተግባር እጅ አልሰጠሁም” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ኣካል ጉዳተኞችና በጡረታ የተገለሉ ሰዎች እራሳቸውን መጣል እንደሌለባቸው ይመክራሉ፡፡ መንቀሳቀስ ለጤናም አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም፡፡ ለበርካቶች ሙያቸውን እንደሚያስተምሩ የተናገሩት ወታደር መለቆ አንዳንዶች ምክራቸውን ሲቀበሉ አንዳንዶች ደግሞ ስራው እጅ ይበላል በማለት እንደሚያሾፉባቸው ነው የነገሩኝ፡፡ እሳቸው ግን ስራን እንደማይንቁ ነው የተናገሩት፡፡ ከሚያገኙት ገንዘብም ለነገ ማለቱን አልዘነጉትም፡፡ ሰርቶ ለሆድ ብቻ ማለቱም ተገቢ አለመሆኑን ይመክራሉ፡፡ ከሚያገኙት የዕለት ገቢ በአስራ አምስት ቀን 50 ብር ይቆጥባሉ፤ በሳምንት ደግሞ 50 ብር ዕቁብም ይጥላሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ከእለት እለት ከጉርሳቸው ነው፡፡ “ዛሬ ላይ ኑሮ ከባድ ነው፡፡ ካልተሰራ ችግሩ ይገዝፋል፡፡ ስድስት ሰው አስተዳድራለሁ፡፡ ካልተሰራ አንድም ሰው ማስተዳደር ይከብዳል፡፡ ለመስራት አልቦዘንኩም፡፡ የማገዶ እንጨትም አጠገቤ መድቤ እሸጣለሁ” ነው ያሉት፡፡ በውትድርና ዓለም በርካታ ችግሮችን እንዳሳለፉ ወደ ኋላ መለስ ብላው ያስታውሳሉ፡፡
ውሃ ሲባል ሲጋራ፣ ምግብ ሲባል ውሃ፣ መሳሪያ ሲባል ውሃ፣ ጥይት ሲባል ሲጋራ እየተላከ ሠራዊቱ ላይ ይደርስ የነበረው አሻጥር ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ለሀገር ሲባል የተከፈለ ዋጋ በመሆኑ ቅር ባይሰኙም ችግሩን ግን ይኮንናሉ። ይሁን እንጂ ከሞት በመትረፋቸው እድለኛ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በህይወት ኖረው እራሳቸውን በማስተዳደራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ነው በነበረን ቆይታ የገለጹልኝ፡፡ በጡረታ 2 ሺህ ብር የሚያገኙ ሲሆን ሰርተው በሚያገኙት ተጨማሪ ሀብትም ኑሯቸውን ይደጉማሉ፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ