በአብርሃም ማጋ
የ78 ዓመቱ አዛውንት በርዕሱ የተገለፀውን ሀሳብ የተናገሩት በሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ 2-07 ቀበሌን በመሩበት ወቅት የፈፀሙትን ተግባር በማስታወስ ነበር፡፡ ሀሳባቸውን ግልፅ ሲያደርጉ ወንጀለኞችን በነፃ እንዲለቀቁ ለማድረግ እንዳልሆነም ያብራራሉ፡፡ ችግር የደረሰበት ባለጉዳይ እሳቸው ጋር ቢያመለክት ተከሳሹን አስጠርተው ጉዳዩን ያጣራሉ፡፡
በቀጣይ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ጉዳዩ በባህላዊ ሽምግልና እልባት እንዲያገኝ ማመቻቸት ነው፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች በባህላቸው መሠረት በእርቅ እንዲጨርሱትም ጉዳዩን ይሰጧቸዋል፡፡ በዚሁም ማንኛውም ዓይነት ግጭት በሰላማዊ መንገድ ተጠናቅቆ እርቅ እንደሚፈጸም ይናገራሉ፡፡
በመቀጠልም በአድቬንቲስት ቤተክርስቲያን ከወንጌላዊነት ጀምረው በትልቅ ሐላፊነትና መሪነት አገልግለዋል። በማህበራዊ ህይወታቸው ይበል የሚያሰኝ ሥራ ሠርተዋል። በዚህ መነሻ መልካም ተሞክሯቸውን ልናስነብባችሁ ወደድን፤ መልካም ንባብ፡፡
አቶ ዮሴፍ ሜላ በ1938 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡ የትውልድ ቦታቸውም በወላይታ ዞን ዱጉና ፋንጐ ወረዳ፣ ቢጠና በሚባል ከተማ ነው፡፡ አባታቸው በወቅቱ ወንጌላዊ በመሆናቸው ለወንጌል አገልግሎት ወደ ኩየራ አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን ሲዛወሩ አቶ ዮሰፍም በጨቅላነታቸው ወደዛ ተወሰዱ፡፡ በአካባቢው የሚነገረውን የኦሮምኛ ቋንቋ የአፍ መፍቻ አደረጉት፡፡ እድገታቸውም እዚያው ሲሆን ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍልም በቤተክርስቲያኑ ሥር በተከፈተው ት/ቤት ተምረዋል፡፡
ከዚያም ወደ ሐዋሳ ከተማ ተዛውረው ከ7ኛ እስከ 11ኛ ሐዋሳ ታቦር ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እየተማሩ እያሉ ወቅቱ በደርግ መንግስት እድገት በህብረት እውቀትና የሥራ ዘመቻ ታወጀ፡፡ ጉዳዩ እሳቸውን ስለሚመለከታቸው በዘመቻው ተሳተፉ፡፡ ከዚያም ከአንድ ዓመት ግዳጅ በኋላ ተመልሰው 12ኛ ክፍልን አጠናቀቁ፡፡
በወቅቱ ወደ ትዳር ዓለም ገብተው ስለነበር ሥራ መቀጠሩን እንደ አማራጭ ወሰዱ። በመሆኑም ደቡብ ኢትዮጵያን በሚያቅፍ በአድቬንቲስት ቤተክርስቲያን በ170 ብር በወንጌላዊነት ተቀጠሩ፡፡ በወንጌላዊነት ለተወሰኑ ዓመታት ከሠሩ በኋላ በእድገት የትምህርት ክፍል ሃላፊ ሆኑ፡፡ በወቅቱ ደቡብ ኢትዮጵያን የሚያቅፍ ለአብነት በያቤሎ፣ በከምባታ፣ በወላይታ፣ በአርሲ እስከ ዝዋይ ድረስ በቤተክርስቲያኑ ሥር የሚተዳደሩ መ/ ቤቶች እንደነበሩ አቶ ዮሰፍ ያብራራሉ። በትምህርት ክፍል ሃላፊነት ለ7 ዓመታት ከሠሩ በኋላ አሁንም በእድገት መጋቢነት ክፍል ሃላፊ ሆነው ተመድበው ለ8 ዓመታት ያህል ሠርተዋል፡፡
በመቀጠልም የደቡብ ኢትዮጵያ አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን መሪ ሆነው ለ2 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በጡረታ ተገልለዋል።
አቶ ዮሴፍ በወቅቱ በአድቬንቲስት ቤተክርስቲያን ውስጥ ቋሚ መንፈሳዊ ሥራቸውን እየሠሩ እያሉ በህብረተሰቡ ዘንድ በነበራቸው ትልቅ ከበሬታ በቀድሞው አጠራር 2-07 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው በህዝብ ተመርጠው ሊቀመንበር ሆኑ፡፡
በዚሁም በርካታ ተግባራትን ፈጽመዋል። የቀበሌውን ጽ/ቤት ያሠሩት በህዝብ መዋጮ ሳይሆን በአካባቢው በሚገኙ ባዶ መሬቶች ላይ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ድንች፣ ስኳር ድንች በማስተከል በተገኘ ገቢ ነበር፡፡ በዋናነት ግን በህዝብ መብቶች ዙሪያ ጥሩ ሥራ ሠርተዋል። ህብረተሰቡን አድሎአዊነት በሌለበት ሁኔታ በእኩልነት፣ በሐቀኝነት፣ በታማኝነት አገልግለዋል፡፡
በወቅቱ አባታዊ ሊቀመንበር ለመሠኘት የበቁት በተጠቀሱት ጉዳዮች ነው፡፡ አባት ልጆቹን ሁሉ በእኩል ዓይን እንደሚያያቸው ሁሉ እሳቸውም ዘመዴ ነው፣ አማቼ ነው፣ ወንድሜ ነው ሳይሉ በተረጋጋና በሰከነ ሁኔታ አስተዳድረዋል፡፡ በልበ ሙሉነት ጉዳዮችን በጥልቀት መርምረው ትክክለኛ ውሳኔም ሰጥተዋል፡፡
በወቅቱ የተጣላ፣ የተሰረቀ፣ የተመታ፣ የተፈነከተ፣ ወዘተ… እሳቸው ዘንድ ቢመጣ ጉዳዩን በዘዴ ጠይቀውና መርምረው ይረዱ ነበር፡፡ በመሆኑም ባህላዊ የእርቅ ዳኝነት ሥርዓት ከዘመናዊ ፍትህ አሰጣጥ ባላነሰ መልኩ መፍትሔ እንደሚያስገኝ ስለተረዱ ጉዳዩ በሽማግሌዎች እንዲፈታ ያደርጉም ነበር፡፡
ይህ ትልቅ እሴት እስከ ነፍስ ግድያ ድረስ ያሉ ወንጀሎችን የሚዳኝ ሥርዓት በወቅቱ ይታዩ ለነበሩ ችግሮች መፍትሔ ሰጥቷል ይላሉ፡፡ በዚህ መነሻ ነው “አንድም ሰው ፖሊስ ጣቢያና ፍርድ ቤት ልኬ አላውቅም” ሲሉ የተደመጠው፡፡
ከአመራሮቻቸው ጋር ሆነው ህዝቡን በማስተባበርና በማሳተፍ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብዙ ችግሮች ባያጋጥማቸውም አንድ ለማንሳት የሚፈልጉት ክስተት ነበር፡፡
ወቅቱ ኢህአፖ የተባለው የፖለቲካ ድርጅት ገኖ ስለነበር የወጣቶች ማህበር አመራሮች በየቤቱ እየገቡ የኢህአፖ አባል አለ በማለት አሳብበው ብዙ ቤቶችን ይፈትሹ ነበር፡፡ ነገር ግን ይኖራል የተባለው ግለሰብ ሳይኖር ሲቀር ቤት ያፈራውን ሁሉ ዘርፈው ይወጣሉ፡፡ እስከ 3 ሺህ ብር ድረስ የተዘረፉ ግለሰቦች መኖራቸውንም ያብራራሉ፡፡ በወቅቱ የተጠቀሰው ገንዘብ አንድ ቤት መግዛት እንደሚችል በሙሉ እምነት ይናገራሉ፡፡
በአንድ ግለሰብ ቤት የተጠቀሰው ጉዳይ ተከስቶ ጉዳዩ ደርሷቸው ክትትል አድርገው በቁጥጥር ስር አውለዋቸው ከመረመሩ በኋላ ደርሰውበት ለባለቤቶቹ ብሩን አስመልሰዋል።
በዚሁም እነዚህ ወጣቶች ቂም ይዘውባቸው ኖሮ ማንነቱ የማይታወቅ፣ የድርጅቱ አባል ያልሆነ የህዝብ ውግንና የሌለው ነው ብለው አሳደሙባቸው፡፡
ከዚህ ጋር አያይዘው ያቀረቡት ማስረጃ አርሶ አደሮች በህገ ወጥ መንገድ / በኮንትሮባንድ/ ጭነው ሲሄዱ ያገኘውን ቡና ዘርፎ ለራሱ ተጠቅሟል የሚል ክስ ነበር፡፡
በዚህ መሠረት ሥርዓቱ ሥርቆት የሚባል ነገር ሲነሳ ትእግስት የሌለው በመሆኑ እውነት መስሏቸው ለ24 ቀናት ታስረው ምርመራ ተካሄደባቸው፡፡ ነፃ ሰው ነው ተብለው ተለቅቀው እንደገናም በህዝብ ጩኸት ወደቦታቸው ተመልሰው ለተወሰኑ ዓመታት አገልግለዋል፡፡
በዚያን ወቅት የህዝቡ ስሜት ምን እንደነበር ጠይቀናቸው ነበር፡፡ የገለፁልን ምላሽ ህዝቡ እሳቸው በእንደዚህ ዓይነት ተልካሻ ድርጊት ውስጥ እንደማይገቡ መመስከሩን ይናገራሉ፡፡
እንዲያውም በታሰሩባቸው ቀናት ከራሳቸው ቤት አንድም ቀን ስንቅ ተወስዶላቸው እንደማያውቅ ይገልፃሉ። ህዝቡ ራሱ ከቤቱ ተራ በተራ እያዘጋጀ ስንቅ ይሰጣቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። እሳቸውም ቢሆኑ ለአካባቢው ህብረተሰብ ከፍተኛ ፍቅር፣ ምስጋና እና አክብሮት እንዳላቸው ደጋግመው ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ውጭም አቶ ዮሴፍ ሰዎችን በማስታረቅ ረገድ ላቅ ያለ ማህበራዊ ተሳትፎ አላቸው፡፡ በባለትዳሮች እና በጐረቤታሞች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ አለመግባባትና ጥል የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በተረትና ምሳሌያዊ አነጋገር በማሳመን ችግሮችን ይፈታሉ፡፡
በአብዛኛው እሳቸው የያዙት እርቅ እንደሚሳካላቸውም ገልፀዋል፡፡ ለአብነትም ከዓመታት በፊት በሀዋሳ ከተማ በተፈጠረው አለመግባባት ቅራኔ በነበረባቸው አካላት መካከል እርቅ እንዲደረግ ከሌሎች ሽማግሌዎች ጋር ሆነው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡
ከዚህ ውጭም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በዓመት አራቴ በሚከበሩ በዓላት ወቅት የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ በማስተባበር በዓላቱ ላይ የጋራ ትስስር እንዲኖር በማድረግም ማህበራዊ መስተጋብርን በማሳደጉ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል፡፡ አሁንም እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መስተጋብሮች አንዱ ቅርጫ ነው፡፡
ቀደም ሲል በዓሉ ሲደርስ በአራጆች ይከሰት የነበረውን ብዝበዛ ለማስቀረት ችግር ፈቺ የሆነ መላ ፈጥረዋል፡፡ በሬው ከተገዛበት ዋጋ በእጥፍ ተጨምሮ የሚከፈለውን ዋጋም አስቀርተዋል፡፡ 12 ሰዎችን አደራጅተው፣ ኮሚቴ አዋቅረው ሰብሳቢ፣ ፀሐፊና ገንዘብ ያዥ አስመርጠው በዓሉ ሳይደርስ በየወሩ የተወሰነ ገንዘብ እያዋጡ ተቀማጭ ያደርጋሉ ቀደም ሲል የከብት ዋጋ እጅግ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ከ10 ብር የማይበልጥ ብር በየወሩ እያስቀመጡ ለበዓላቱ ማረድ ጀመሩ። ተገቢ ሥጋ በዝቅተኛ ገንዘብ ማግኘት ቻሉ፡፡
በየጊዜው የከብት ዋጋ እየጨመረ ሲመጣ ወርሃዊ መዋጮአቸውን እየጨመሩ ከ3 ዓመታት በፊት 100 ብር አደረጉ፡፡ በዚህም እጅግ ተጠቃሚና ትርፋማ ነበሩ፡፡ ከ3 ዓመታት ወዲህ ግን ወርሃዊ መዋጯአቸውን 2ዐዐ ብር አድርገው ዓመት በዓላቱን ሳይቸገሩ እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡
የዘንድሮውን አዲስ ዓመት በዓል የተቀበሉት 28 ሺህ ብር በገዙት በሬ ነበር። ከ3 ወር በፊት በተጠቀሰው ገንዘብ የገዙትን በሬ በአድቬንቲስት ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ በማደለብ ያቆዩታል፡፡ ግቢው ሰፊና ብዙ ሳር ያለበት በመሆኑ ሳሩን እየበላ እንዲቆይ ያደርጉታል፡፡ ለበሬው ማደለቢያነት የሚያገለግሉ ግብአቶችን፣ በቆሎ፣ ፍሩሽካ የመሳሰሉትንም በመጠኑ ገዝተው አብዛኛውን በሳር ብቻ ቀለቡት፡፡ ብዙ ውጪ ሳያወጡ በሬው ደልቦ በእጥፍ ዋጋ የሚተመን ደረጃ ይደርሳል፡፡ ማለትም በ28 ሺህ ብር የገዙት በሬ የ56 ሺህ ብር ግምት ይደርሳል፡፡ በቀጣይ ለሚከበረው መስቀል በዓል ከ3 ወር በፊት በ30 ሺህ ብር የገዙት በሬ በጣም ወፍሮ እንደሚገኝም ገልፀውልኛል፡፡
ዓመት በዓሉን ቀደም ሲል እያንዳንዱ ቤት እየተጠራሩ እየዘሩ ያከብሩ ነበር፡፡ አሁን ግን እያንዳንዱ ግለሰብ ከቤተሰቦቹ ማለትም ከልጆቹ፣ ከልጅ ልጆቹ እና ከአማቾቹ ጋር ተሰባስቦ ይመገባል፤ ይጨዋወታል፡፡
ቀደም ሲል የአባላቱ ቁጥር 12 የነበረው አሁን ወደ 6 ዝቅ ማለቱን የጠቀሱት አቶ ዮሴፍ ይህም በሞትና በዝውውር ምክንያት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
አቶ ዮሴፍ የቋንቋ ችሎታቸውም የሚደነቅ ነው፡፡ እንግሊዝኛ፣ ኦሮምኛ፣ ወላይትኛ፣ ሲዳምኛ እና ከምባትኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ።
ወደ ትዳር ዓለም የገቡት በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲሆን 4 ወንድ 5 ሴት ልጆች አፍርተዋል፡፡ ወንዶቹ ልጆቻቸው በግል ድርጅት ይሠራሉ፡፡ ሴቶቹ የመንግስት ሠራተኞች ሲሆኑ ሁለቱ የቤት እመቤቶች ናቸው፡፡ 11 የልጅ ልጆች አይተዋል፡፡
የመስቀል በዓል አከባበርን በተመለከተም፦ “ዘመን መለወጫን ያደረሰው ፈጣሪ አምላክ ነውና ለዚህ ያበቃን አምላክ ምስጋና ይድረሰው፡፡ ዘመኑ የደስታ፣ የሰላም፣ የፍቅር እና የጥጋብ እንዲሆን እመኛለሁ” የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ