ባላንጣዎችን ያሳፈረ ቆራጥነት

(የአባይ ወግ)

በኢያሱ ታዴዎስ

ምድሪቱ ጽልመቱ ተገፎ ብርሃን መመልከት ጀምራለች። ይኸው ብርሃን ደግሞ ከዓመት ዓመት እየደመቀ ከሀገሪቱ አልፎ አህጉሪቱን ሊያዳርስ አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ይገኛል። በብዙዎች ዘንድ ስለሀገሪቱ የነበረው ጨለምተኛ አስተሳሰብም ተቀይሯል። አሁን የብርሃን ምልክት ሆና ራሷን ከጨለማ ነጻ የምታወጣበት ዘመን ላይ ተገኝታለች። እድሜ ለአባይ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እነሆ አራተኛ ሙሌቱ ላይ ደርሶ በአዲሱ ዓመት የምስራች ይዞ ብቅ ብሏል። አባይ አሁን የትካዜ ጉዞው አብቅቶ የህልም ሳይሆን የእውን እንጀራ ሊያቋድሰን መሶቡን ከፍቶልናል። ከእንግዲህ ለዘመናት እንጀራችን ሊሆነን የሆዱን ፍሬ ሰጥቶናል። አባይ ከድህነት መውጫችን መሰላል ሆኖናል። ብቻ ብዙ ገጸ- በረከት ተሸክሞ ካሰብነው ከፍታ ሊያደርሰን ጉዞውን ጀምሯል።

የአባይ አስደናቂ ታሪክ የተሰራው ባለፉት 12 ዓመታት ነው። የአቅሙን ያህል አልለገሰንም በሚል ቁጭት የተጀመረው ግንባታ ዛሬ ፍሬው ብርሃን ሆኖ እየታየ ነው። ይህ ሁሉ ግን በታላቅ መስዋዕትነት የተገኘ ነው።

አባይ ለልማት እንዳይውል ብዙ ጠላቶች ተነስተውበታል። ጠላቶቹም ብቅ ያሉት ዛሬ ሳይሆን ያኔ ከዘጠና ዓመታት በፊት ነው። በአውሮፓዊያኑ 1929 ግብጽ እና እንግሊዝ የቅኝ ግዛት ውል የተሰኘውን ስምምነት ተፈራረሙ። እንግሊዝ ስምምነቱን የፈረመችው ኡጋንዳ፣ ኬኒያ፣ ታንዛኒያ እና ሱዳን የመሳሰሉትን የተፋሰሱ ሀገራት በመወከል ነበር። ስምምነቱ ግብጽን ሙሉ ለሙሉ ከአባይ ወንዝ ተጠቃሚ የሚያደርጋት፣ በአንጻሩ ወንዙ ከሆዷ የሚወጣውን ኢትዮጵያ ከነመፈጠሯ የዘነጋ ነበር። እንግሊዝ በብልጠት ሌሎቹን ሀገራት ወክላ የመፈረሟ ምስጢርም ግብጽ በምታገኘው ጥቅም ውስጥ የራሷን ጥቅም ለማስከበር ነበር። “ጅብ የማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል” እንደ ሚለው የአበው ተረት፥ ብልጠቷ ገለልተኛ ሆኖ የተመለከተን አካል በእጅጉ የሚያበሳጭ ነበር። ይሄ አካሄድ ሁለቱን ሀገራት የአባይ ባላንጣ ሆነው ኢትዮጵያ ላይ እንዲነሱ አደረጋቸው።

ይህ የብልጠት አካሄድ ዳግም በ1959 በተፈረመ ሌላ ስምምነት ተደገመ። በግብጽና ሱዳን መካከል የተካሄደ የቀድሞውን የሚደግፍ ስምምነት ነበር። አሁንም የአባይ ባለቤቷን ኢትዮጵያ ባይተዋር አድርጓል። በአንጻሩ ግብጽ 55.5 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር (66 በመቶ)፣ ሱዳን ደግሞ 18.5 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር (22 በመቶ) የውሃ ድርሻ ከወንዙ እንዲኖራቸው መብት የሰጠ ነበር – ስምምነቱ። የቀረው 12 በመቶ የውሃ ድርሻ በትነት የሚያልቅ ነበር።

እንግዲህ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንደሚባለው ግብጽ ከፍተኛውን የውሃ ድርሻ ለራሷ አድርጋ፣ ጎረቤቷን ሱዳንን አፏን ለማዘጋት የተወሰነ ድርሻ ሰጥታት አባይን ለብቻዋ ለመጠቀም ትማስን ጀመር። በወቅቱ ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ መላቀቅ የተሳናት እንግሊዝ ከወንዙ እንደ ጥጥ ያሉ ምርቶችን ትጠቀም ነበርና ፊትአውራሪ የስምምነቱ አቀንቃኝ ሆነች።

ይሁን እንጂ በ1999 ሁሉም የናይል ተፋሰስ ሀገራት ከወንዙ እኩል ተጠቃሚነት ሊኖራቸው ይገባል በሚል 10 ሀገራት የጋራ ጥምረት ፈጠሩ። ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሱዳን፣ ቡሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኬኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ።

የጥምረቱ ተልዕኮም በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ቀጠናዊ ሰላም፣ የውሃ ደህንነት እና ማህበረሰባዊ ኢኮኖሚን ማሳደግ ነው። በተጨማሪም እንደ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ያሉ አባል ሀገራት መስኖና ተፋሰስ በመጠቀም የጎርፍ አደጋን መከላከል እንዲሁም በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች ተጠቃሚነት ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር።

ጥምረቱ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል እንዲኖር በተለያዩ ጊዜያት ባደረገው ጉባዔ አጽንኦት ቢሰጥም የግብጽ የእጅ አዙር አካሄድ ግን የቅኝ ግዛት ዘመኑ ውል ዳግም እንዲያንሰራራ ነበር። በዚህ መሃል ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ነቃች። ለዘመናት ከገዛ ሆዷ ወጥቶ እምብዛም ጥቅም ሳይሰጥ ወደ ጎረቤት ሀገራት እየፈሰሰ እህል ውሃ የሆናቸው አባይ ለምን ለእኔም ብርሃን አይሆነኝም ስትል በቁጭት ልትሰራ ተነሳች።

ኢትዮጵያ ይህን ስትወስን አስቀድሞ አስሮ የያዛትን የግብጽ የቅኝ ግዛት ዘመን ውል አሻፈረኝ በማለት ነበር። ዜጎቿን አሰባስባ በአፍሪካ ግዙፍ የተባለውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ እውን ለማድረግ ወገቧን ጠበቅ አድርጋ መገንባት ጀመረች። ይህ ለአባይ ልጆች ዳግም የመወለድ ያህል ነበር።

አባይ ከወንዝነት አልፎ አንድም ብርሃን፣ በሌላ በኩል እንጀራ ሊሆን አዲስ ጉዞ ተጀመረ። በዚህ ወቅት ለሀገር አንድነት ዘብ በመቆም የሚታወቀው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያለስስት እጆቹን ግድቡን ለመገንባት ዘረጋ። የኢትዮጵያን አየር ሁሉ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ተቆጣጠረው።

ይህን ጊዜ ሁኔታው አላምር ያላት ግብጽ ሱዳንን አስተባብራ ኢትዮጵያ በዓይኔ መጣች ስትል አምጓሮ መፍጠር ጀመረች። ለናይል ተፋሰስ ሀገራት ጥምረት አባይ ከእኔ ሌላ ለአሳር ስትል ራስ ወዳድ አቋሟን ማንጸባረቅ ተያያዘች። በጎን ሱዳንንም እያነሳሳች ግድቡ እንዳይገደብ ጥረቷን ቀጠለች።

ግብጽ ሙሾ ማውረጃ ሃሳቧ ያደረገችው የሀገሪቱን 98 በመቶ የውሃ ፍላጎት የሚያሟላው ናይል፣ አባይ የሚገደብ ከሆነ መጠኑ ቀንሶ ህልውናዬ አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል ነበር። የህዳሴ ግድብ ግንባታው ሲጀምር የግብጽ ዓላማ ግንባታው እንዳይካሄድ ማድረግ ነበር።

ሱዳንም ብትሆን የግብርናዬ የጀርባ አጥንት የሆነው አባይ የሚገደብ ከሆነ ይዘቱና ይዞት የሚገባው ለም አፈር በእጅጉ ቀንሶ ድርቅ ያስከትልብኛል የሚል ከግብጽ የተኮረጀ ግትር አቋም ይዛ ተነሳች።

ግብጽ ይህ ሳይበቃት የአረቡንና የምዕራቡን ዓለም ሚዲያዎች ለእሷ ወግነው እንዲሟገቱላት አሳምና ጩኸቷን የአደባባይ አደረገችው። ወትሮ የኢትዮጵያ ነገር የማይጥማቸው ምዕራባዊያን ተመራማሪዎችና የፖለቲካ ምሁራን ሳይቀሩ ከግብጽ ጋር ሙሾ ማውረዱን ተያያዙ። ጉዳዩም ትልቅ የጂኦ ፖለቲካ ቅራኔ መነሻ ሆኖ በመላው ዓለም ተስተጋባ።

ኢትዮጵያም ጠላቶቿ አየል አሉ። እርሷ ግን የሆዷን በሆዷ ይዛ ግንባታውን ቀጠለች። ነገሮች ያንኑ ያህል እየከረሩ ሲመጡ የውስጥ ችግሮቿን መፍታት ላይ የተጠመደችው ኢትዮጵያ የመንግስት ለውጥ ተደረገባት። ይህን ጊዜ ግብጽ እና ሱዳን የአባይ ጉዳይ ይረግባል የሚል እምነት በውስጣቸው አደረ።

ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ሆነ። የለውጡ መንግስት በግድቡ ግንባታ ላይ የነበረውን ክፍተት በማረም በአዲስ ጉልበት ወደ ግንባታው ገባ። ብዙ ነገሮች ተቀያየሩ። በየዓመቱ በክረምት ወራት ፍሰቱ የሚጨምረውን ወንዙን ለግድቡ ሙሌት ለመጠቀም ውጥን ተይዞ ገቢራዊ መሆን ጀመረ።

ግብጽ እና ሱዳን ለቅሷቸው በእጥፍ ጨመረ። አፍሪካን ረግጠው ለምዕራባዊያኑ ያደላሉ የተባሉትን እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያሉ ተቋማትን ደጅ ይጠኑ ጀመር። ኢትዮጵያም ቅራኔያቸውን ችላ በማለት ግንባታዋን አጣደፈች። ግትርነቷ እንደማያዋጣ የተገነዘበችው ግብጽ ቃሏን አጠፈችና “ግንባታው ይሁን፤ የውሃ ሙሌቱ ግን ከአስር እስከ ሀያ ዓመታት ባሉ ጊዜያት ይከናወን” ስትል በሌላ አቋም ብቅ አለች።

ግብጽ በምሁራኖቿና በሚዲያዎቿ ታግዛ ኃያላን መንግስታት፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት አብረው እንዲያላቅሷት ጉትጎታ አደረገች። ይሄኔ ነበር የኢትዮጵያ ጠላት የበዛው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ግብጽን ለማስደሰት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብዙ ጊዜ መከረ።

የአውሮፓ ህብረት እርዳታ ላለመስጠትና ማዕቀብ ለመጣል ዳዳው። የገንዘብ ተቋማትም ጅራፋቸውን አነሱ። አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና እስራኤል ማዕቀብ በመጣል ሰበብ በእጅ አዙር ጫና ማሳደራቸውን ገፉበት። ጭራሽ አሜሪካ በወቅቱ ፕሬዝደንቷ ዶናልድ ትራምፕ በኩል ግብጽ የህዳሴውን ግድብ ታፈርሰዋለች ስትል ዛቻ አዘል መልዕክቷን አስተላለፈች።

ይህ ሁሉ ጫና ግን ኢትዮጵያን ሊያስቆማት አልቻለም። ይበልጥ አበረታት እንጂ። ኢትዮጵያ ደጋግማ በየዓመቱ የውሃ ሙሌት ማድረግ ቀጠለች። የግድቡም ግንባታ ከታሰበው በላይ ተፋጥኖ ይኸው የመጨረሻ ምዕራፉ ላይ ይገኛል። አሁን የጸጥታው ምክር ቤት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ግብጽ እና ሱዳን ዛቻና ማስፈራራት መና ሆኖ ቀርቷል። ግብጽ እና ሱዳን ለነገሩ እጅ መስጠታቸውን በሚያሳብቅ መልኩ አማራጭ ያደረጉት በቅርቡ ያካሄዱት የሶስትዮሽ ስብሰባ ነበር። ከዚያ ውጪ እንደ በፊቱ የጦርነት ነጋሪት ለመጎሰም አልደፈሩም።

አሁን የአባይ ግድብ ቅኔ በ12 ዓመታት ውስጥ ፍንትው ብሎ ተፈቷል። የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 92.3 በመቶ ደርሷል። በተያዘው አዲስ ዓመት ተጨማሪ 5 ተርባይኖችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ አድርጓል።

አምስቱ ተርባይኖች ወደ ስራ ሲገቡ ሀገሪቱ አሁን ላይ ያላትን 4 ሺህ 818 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት መጠን ከፍ እንደሚያደርገውም ተገልጿል። የተርባይኖቹ የኃይል መጠንም የበለስ፣ የግልገል ጊቤ አንድና ሁለት፣ እንዲሁም የተከዜ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከሚሰጧቸው አማካይ 1 ሺህ 180 ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጩ ይጠበቃል።

የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ በ13ቱ ተርባይኖች 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብሄራዊ የኃይል ቋት ይቀላቀላል ተብሏል። ይህም ሀገሪቱን በኃይል አቅርቦት በአፍሪካ ቀዳሚ ያደርጋታል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተምሳሌትነቱ ዘበብዙ ሆኗል። የኢትዮጵያዊያን አይበገሬነት፣ ቆራጥነትና የዓላማ ጽናትን በጉልህ የሚያንጸብርቅ መሳሪያም ነው።