የግብርናው ዘርፍ ለጂዲፒ ካለው ድርሻ አኳያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢንደስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች ተበልጧል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የግብርናው ዘርፍ ለጂዲፒ ካለው ድርሻ አኳያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢንደስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች ተበልጧል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የግብርናው ዘርፍ ለጂዲፒ ካለው ድርሻ አኳያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢንደስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች ተበልጧል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

እየተካሄደ ባለው 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ፣ በምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢኮኖሚ ማሻሻያ በየዘርፎቹ ስለመጣው ለውጥ ሲናገሩ ግብርና እና ኢንደስትሪውን አያይዘው አንስተዋል፡፡

በዚሁም ማብራሪያቸው በኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጥ በተሰሩ ሥራዎች የኢትዮጵያ ጂዲፒ 210 ቢሊየን ዶላር መድረሱንና ይህም ከሰሃራ በታች ከሚገኙ ሀገራት ከደቡብ አፍሪካ እና ከናይጄሪያ በመቀጠል ሶስተኛው ትልቁ ኢኮኖሚ መሆን መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ዕድገት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዕድገቶቹን በዘርፎች ለይተው ያቀረቡ ሲሆን በዚህም መሰረት ግብርናው በዚህ ዓመት 7.7 በመቶ ዕድገት እንደሚያመጣ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ለረጅም ጊዜ የኢኮኖሚክ ትራንስፎርሜሽንን ግብርና መር ከሆነው ወደ ኢንደስትሪ መር ለመቀየር የታቀደው ዕቅድ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ዓመት መጠነኛ ሽግሽግ ማድረጉን ነው ያነሱት፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ግብርና አሁን ያለው የጂዲፒ ድርሻ 31.4 በመቶ ሲሆን በዚህ ዓመት 7.7 በመቶ ዕድገት እንደሚያመጣ ነው የሚጠበቀው፡፡ ኢንደስትሪው (ማኑፋክቸሪንግና ኮንስትራክሽንን ጨምሮ) በጂዲፒ ውስጥ ያለው ድርሻ 31.8 ሆኗል፡፡ በኢንደስትሪው በዚህ ዓመት የሚጠበቀው ዕድገት 12.3 በመቶ ነው፡፡

የአገልግሎት ዘርፉንም በተጓዳኝ ያነሱ ሲሆን አጠቃላይ ለጂዲፒ ያለው ድርሻ 33.8 በመቶ መሆኑንና በዚህ ዓመት ወደ 9.9 በመቶ ዕድገት እንደሚያመጣ ይጠበቃል ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡

በዚሁ መሰረት ግብርና ለመጀመሪያ ጊዜ በአጠቃላይ ኢኮኖሚያችን ሶስተኛ ስፍራን ለመያዝ መገደዱን አንስተዋል፡፡ በአንጻሩ ኢንደስትሪው በታሪካችን ከግብርና የላቀ ድርሻ በመያዝ መሪ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አገልግሎት ዘርፉ ደግሞ ከኢንደስትሪ በመቀጠል በሁለተኝነት ለኢኮኖሚው ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ዘንድሮ ያቀድነውን ዕቅድ ስናሳካ ደግሞ ሽግሽጉ በዚያው ልክ እየሠፋ ይሄዳል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በየዘርፉ በኢኮኖሚው የመጣውን ለውጥ አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኢያሱ ታዴዎስ