በደረሰ አስፋው
የዛሬው ባለታሪካችን የዛሬ 40 ዓመት ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስቃኙናል፡፡ ለሀዋሳ ከተማ ዕድገት አሻራ በመጣል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ካበረከቱ የቀድሞ ማዘጋጃ ቤቱ ሹም ጋር ጥቂት ቆይታ አድርገናል በመምህርነት ስራ ጀምረው በሀዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ሹም እና በቀድሞው ሲዳሞ ክፍለ ሀገር በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች በመዘዋወር ህዝብንና ሀገርን አገልግለዋል፡፡
ጡረታ እስከ ወጡበት ጊዜ ድረስ በመንግስት ስራ ብቻ ከ30 ዓመታት በላይ እንዲሁም በተለያዩ የግል ተቋማትም 20 ዓመታት ሠርተዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ተክሉ ቢራቱ ይባላሉ። በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር መናኸሪያ ክፍለ ከተማ ገነት መንደር ነዋሪ ናቸው፡፡ ትውልድና እድገታቸው በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ልዩ ስሟ ጨላ በምትባል የገጠር ቀበሌ ነው። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአካባቢው በሚገኝ ዳጨ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ከፊደል ቆጠራ እስከ ዳዊት መድገም ተምረዋል፡፡ ወላጅ አባታቸውን በሞት በመነጠቃቸው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ከአያታቸው ጋር መኖር ጀመሩ፡፡
አሳዳጊያቸው በስራ ምክንያት ከአዲስ አበባ ወደ ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ሲንቀሳቀስ እሳቸውም በዲላ፣ ፍስሃ ገነት፣ ጨለለቅቱ፣ እና ሌሎች ስፍራዎች ተንቀሳቅሰው ኖረዋል፡፡ በ1951 ዓ.ም አጎታቸው ለትምህርት ከሄዱበት ከአሜሪካ ሲመጡ አቶ ጌታቸው የሳቸው ተፈላጊ ሰው ሆኑ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ያቋረጡትን ትምህርት የመቀጠል ዕድል አገኙ፡፡ በ1952 ዓ.ም “ነጻነት ጎህ” ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ጀመሩ፡፡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው በ1961 ዓ.ም 12ኛ ክፍልን ጨረሱ፡፡ ዩኒቨርስቲ የሚያስገባ ውጤት ባለማምጣታቸው በአለማያ ዩኒቨርስቲ ለመግባት የነበራቸው እቅድ አልተሳካም፡፡
በ1963 ዓ.ም የቀድሞው ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ገብተው የመማር ዕድል አገኙ። በመምህርነት ሙያ ለአንድ አመት ከተማሩ በኋላ የብሄራዊ አገልግሎት ለመስጠት ለምግብ 175 ብር እየተከፈላቸው በደብረ ዘይት በማስተማር ለአንድ ዓመት አገለገሉ። በ1965 ዓ.ም በዲፕሎማ ከታላቁ ቤተ[1]መንግስት ከንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለስላሴ ዲፕሎማቸውን ተቀበሉ፡፡ ከምረቃው በኋላ ከትምህርት ሚኒስቴር ምደባ ተሰጥቷቸው ወደ ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ተመደቡ፡፡ በወቅቱ በአካባቢው ከወላይታና ይርጋለም ከተሞች በስተቀር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አልነበረም፡፡ ወደ ቦረና ተመድበው ከ1965 እስከ 1969 ዓ.ም በነጌሌ ቦረና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአማርኛና እንግሊዘኛ ቋንቋ መምህርነት አስተምረዋል፡፡
በ1969 ዓ.ም በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ድርቅ በመከሰቱ በአካባቢው ድርቁን ለመከላከል አዲስ መስሪያ ቤት ተቋቋመ፡፡ ለተቋቋመው መስሪያ ቤት ጠንካራ ሰራተኞች ሲመረጡ አቶ ጌታቸው የቦረና እርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኃላፊ ሆነው መስራት ጀመሩ፡፡ የቦረና ሁሉም አውራጃዎች የዕለት ደራሽ አስተባባሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በ1969 ዓ/ም በአካባቢው የሶማሌ ጦርነት ተከሰተ፡፡ አካባቢውም የጦርነት ቀጠና ሆነ፡፡ ፈንጅ በየቦታው ይቀበር ጀመር፡፡ ማንኛውንም ስራ ለመስራት አዳጋች ሆነ፡፡ የእርዳታ ስራው በጦርነቱ ምክንያት ተገታ፡፡ ባለታሪካችንም በዚህ ወቅት በመንግስት ባገኙት የትምህርት ዕድል አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተከታታይ ትምህርት ክፍል ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ፡፡
በ1972 ዓ.ም ሀዋሳ ታቦር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመድበው ማስተማር ጀመሩ፡፡ በ1975 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጀመሩት በተከታታይ ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቁ፡፡ እስከ 1978 ዓ.ም መጨረሻ በሀዋሳ ታቦር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አገልግለዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ በዩኒት መሪነት ባገለገሉበት ጊዜ በተማሪዎችና መምህራን ተወዳጅ መምህር ሆኑ፡፡ ታታሪና ስራ ወዳድ የነበሩት አቶ ጌታቸው በትምህርት ቤት በነበራቸው ትጋት በሌሎችም አይን ውስጥ ገቡ፡፡ ይህም ለሌላ የስራ ኃላፊነት እንዲታጩ ማድረጉ አልቀረም፡፡ በ1978 ዓ.ም የሀዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስፈጻሚ ሆኑ፡፡
በ1979 ዓ.ም ደግሞ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሹም ሆነው ተሸሙ፡፡ እሰከ 1981 ዓ.ም በማዘጋጃ ሹምነት ሀዋሳንና ነዋሪዎቿን አገልግለዋል፡፡ በ1981 ዓ.ም መጨረሻ በድጋሜ የቦረና አስተዳደር ሸንጎ ጸሃፊ ሆነው ተሾሙ። ኢህዴግ ሀገሪቷን እስከተቆጣጠረበት ጊዜ ድረስ መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ እዛው ነበሩ፡፡ ሀዋሳ በነበሩበት ጊዜ ቤተሰብ መስርተው ስለነበር ከቦረና ተመልሰው ሀዋሳ መኖር ጀመሩ፡፡ ይህ ጊዜ ለሳቸው ፈታኙን ጊዜ የተጋፈጡበት ነበር። ካለደመወዝ የቤተሰብ ሃላፊነትን መሸከም አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር። ለሶስት ወራት ካለደመወዝ ቆዩ፡፡ ንብረትን እየሸጡ ኑሮን መግፋት ሆነ፡፡ የሀዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ሹምና የኃላፊነት ቦታዎች ሲያገለግሉ የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ወቅቱ ለህዝብ መብትና ጥቅም መከበር እንጂ ለራስ ጥቅም የሚኖርበት ጊዜ እንዳልነበረም በማስታወስ፡፡ የቤት ኪራይ እየከፈሉ ማንኛውም ሰው የሚኖረውን ኑሮ መኖር ሆነ፡፡ በሂደት ግን ወደ ቀድሞው የመምህርነት ሙያቸው ተመለሱ፡፡ ቀድሞ የነበራቸውን የደመወዝ ደረጃ ትተው በአዲስ ተቀጣሪ በ500 ብር እንዲቀጠሩ መደረጉን በማስታወስ፡፡
በታቦር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ አገለገሉ፡፡ በ1994 ዓ.ም ጡረታ ወጡ። ከጡረታ በኋላ በግል የትምህርት ተቋማት። በአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በመምህርነት ለሁለት አመት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ የትምህርት ኮሌጅ ለ16 ዓመታት ያህል በመምህርነት፣ በዲን እና በአስተዳደር አገልግለዋል፡፡ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን በእግራቸው ላይ ባጋጠማቸው የጤና እክል ከስራው ተሰናበቱ፡፡ በሀዋሳ ከተማ የማዘጋጃ ቤት ሹም ሆነው ባገለገሉበት ጊዜ በርካታ አሻራቸውን የጣሉባቸው ስራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።
“ሰው ስለራሱ ከሚናገር ይልቅ ሌላው ቢናገር ይቀላል” የሚሉት አቶ ጌታቸው አቅማቸው የፈቀደውን መስራታቸውን ነው የተናገሩት። በሰሩት ስራም በሀዋሳ አንገታቸውን ደፍተው እንደማይሄዱ ይገልጻሉ፡፡ በ1978 ዓ.ም የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ቁጥር 36 ሺህ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የህዝብ ፍላጎት ለማሟላት ላይ ታች ይሉ እንደነበር ነው ያጫወቱን፡፡ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሰሩ የከተማዋ ዕድገት ላይ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል፡፡ የከተማዋን ውበት ለመጠበቅ ሲባል በተለያዩ አካባቢዎች ፓርኮችን አስገንብተዋል። ቁጠባ ቤቶችንም እንዲሁ።
የቁጠባ ቤቶች ሀይቅ ዳር አሁንም እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡ የአሞራ ገደል መናፈሻው ለመዝናኛ ምቹ የማድረግ ስራ ያኔ መሰረት መጣሉንም ጠቁመዋል፡፡ የከተማው ነዋሪ በእረፍት ቀኑ እንዲዝናና የመዝናኛ ግብአቶች የማደራጀት ስራዎች መስራታቸውንም ጠቃቅሰዋል፡፡ የነዋሪውን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላትና አስፈላጊ ነገሮችን በቅናሽ ዋጋ እንዲያገኝ የስጋ ቤቶች፣ የዳቦ ቤቶችን በመገንባት ነዋሪውን ተጠቃሚ አድርገዋል፡፡ በከተማው መዋለ ህጻናት፣ የመጀመሪያና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት የትምህርት ሽፋኑን ለማሳደግ ተሰርቷል፤ ዛሬ ለደረሰበት የትምህርት ዕድገትም አሻራ መጣሉን በመጠቆም፡፡
የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የመገበያያ ቦታዎች፣ የመጠጥ ውሃ ግንባታዎች ሌሎች ተጠቃሽ ስራዎቻቸው ነበሩ፡፡ ከዩኒሴፍ ጋር አብሮ በመስራት ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት እንዲስፋፉ አድርገዋል፡፡ ከተማዋ በፕላን የተገነባች ከተማ እንደሆነችም ጠቅሰዋል፡፡ ሌተናል ጀነራል ኢሳያስ ገ/ስላሴ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ በነበሩት በ1960 ዓ.ም ክፍለ ሀገሩ ከይርጋለም ወደ ሀዋሳ እንዲመጣ እንዳደረጉ ይጠቅሳሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ምናልባትም ሀይቁ ለመዝናኛ ተመራጭ ይሆናል የሚል ግምትም አላቸው፡፡ ንጉሱ ሀዋሳ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት እንድትሆን እንደፈቀዱም ይነገራል፡፡ ሀዋሳ ከተማ ለልማት ተግባራት መመረጥ የጀመረችው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እንደሆነም ያስታውሳሉ፡፡
በወቅቱ የሀዋሳ ከተማ በጀት በጣም ትንሽ የሚባል ነበር፡፡ በ1979 ዓ.ም ከአንድ ሚሊዮን ብር ያነሰ ነበር፡፡ በዚህም ቢሆን በርካታ የልማት ስራዎች ይሰሩ ነበር፡፡ ኢንጅነር ተከስተ አድህኖም የሚባሉ ኤርትራዊ የአስመራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ሲቪል ኢንጅነር ስለነበሩ ከርሳቸው ጋር በመሆን በርካታ ስራዎች በከተማው ሰርተዋል፡፡ ፕላኑ ተከልሶ የሀዋሳ ከተማ ድንበር በስተደቡብ ከታቦር ተራራ ጀርባ እስከ ሎቄ መንደር፣ በደቡብ ምስራቅ የአላሙራ ተራራ ግርጌን ይዞ ትንባሆ መኖፖል ድንጋይ ካቡን ይዞ፣ በስተምስራቅ በኩል ጨፌ፣ በሰሜን ደግሞ የጥቁር ውሃን ድልድይ ይዞ እንዲሆን የተደረገውም በዛን ጊዜ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡
የሀዋሳ ከተማ ፕላን ሲዘጋጅ በዋናነት ትኩረት ያደረጉት ማህበራዊ ግንኙነትን፣ የከተማውን ፊዚካል ካራክተርስቲክስ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ነው የሚናገሩት። እስከ አርሲ ነጌሌ የነበረውን ግንኙነትንም ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ፕላን እንደነበርም ነው ያነሱት፡፡ በ1978 ዓ.ም የቀድሞው የሀገሪቷ መሪ መንግስቱ ኃይለማርያም ሀዋሳን ሲጎበኙ በከተማዋ ውስጥ የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት እንዲገነቡ ማድረጋቸውንም ያስታውሳሉ፡፡ ዩኒቨርስቲ እና ሪፈራል ሆስፒታል የተገነባው ያኔ የተያዘውን ዕቅድ መነሻ በማድረግ እንደሆነ ነው የተናገሩት። የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ አለም አቀፍ ውድድሮችን የሚያስተናግድ ስቴዲየም እንዲገነባም የታቀደው ያኔ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ የዱቄት ፋብሪካውና የሴራሚክ ፋብሪካውም መገንባትም ከተማዋ የበርካታ የመንግስት ሰራተኞች መኖሪያ ሆነች።
ይህም በከተማዋ ዕድገት ላይ የራሱን አወንታዊ ተጽእኖ ማበርከቱን ነው አቶ ጌታቸው የገለጹት፡፡ ከተማዋ የዘመናዊ ከተማ መልክ እንድትይዝ እየተደረገ መምጣቱንም በመግለጽ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የንጹህ መጠጥ ውሃ ከርቀት ቦታ ተጠልፎ የመጣው አቶ ጌታቸው የከተማው ማዘጋጃ ሹም በነበሩበት ጊዜ ነው። ጥራቱ እና ንጽህናው ካልተጠበቀ ውሃ ጋር ተያይዞ በሰዎች ላይ የሚሰተዋለውን የጤና እክል ለመከላከል ጥረት መደረጉንም ያነሳሉ። ለ20 ዓመታት ያህል ያገለግላል የተባለ የውሃ ፕሮጀክት እውን ሆነ፡፡ በወቅቱ የከተማዋ ዋና የትራንስፖርት አገልግሎት የፈረስ ጋሪ ብቻ ነበር፡፡ የከተማው መንገድም ቢሆን የጠጠር መንገድ እንጂ የአስፓልት መንገድ አልነበረም፡፡ ከማዘጋጃ ቤቱ መለስተኛ አውቶብሶች ውጭ በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተሸከርካሪ አልነበረም፡፡
ከተማዋ ሁለት ከፍተኛና 14 ቀበሌዎችም ነበሯት፡፡ የጎርፍ ችግር ከተማዋን ይፈትን እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ችግሩን ከመከላከል ጎን ለጎን የሀይቁንም ደህንነት ትኩረት ይሰጠው ነበር ይላሉ፡፡ ለዚህም ሲባል በ2 ትላልቅ ሞተር የሚጠራቀመውን የጎርፍ ውሃ ከደለል እያጣራ ንጹህ ውሃ ብቻ ወደ ሀይቁ እንዲገባ ይደረግ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ ሀዋሳ አሁን ያለችበት ሁኔታ ሲገልጹም የሀዋሳ እድገት የሚደነቅ እንደሆነ ያነሳሉ። ሰፋፊ መንገዶች ተሰርተዋል፡፡ የተሟላ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተስፋፍተዋል። ምቹ የመኖሪያ ከተማ መሆን ችላለች። እሳቸው ከነበሩበት ጊዜ ጋር ሲነጻጸርም የሰማይና የምድር ያህል እንደሆነ ነው የተናገሩት። በህይወት ኖረው ይህን በማየታቸውም ደስተኛ ስለመሆናቸው ነው የገለፁት፡፡ ባለታሪካችን የጡረታ 3 ሺህ 100 ብር ከማግኘት ወጪ በጥቅማጥቅም ያካበቱት ሀብት የላቸውም፡፡
ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ የኔ የሚሉት ቤት እንዳልነበራቸው የተናገሩ ሲሆን ከጡረታ በኋላ እንደማንኛው ሰው ቦታ ተመርተው መኖሪያ ቤት እንደገነቡ ነው የተናገሩት፡፡ ይህ ዛሬ አንገቴን ቀና አድርጌ እንድኖር አስችሎኛል በዚህም ደስተኛ ነኝ” ብለዋል፡፡ ዛሬ ላይ የስድስት ልጆች አባት የሆኑት ባለታሪካችን አቶ ጌታቸው እነዚህንም አስተምረው ለቁም ነገር አድርሰዋል፡፡ ልጆቻቸው ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ 2ኛ ዲግሪ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተምረው የስራ ባለቤት ሆነዋል፡፡ ሀዋሳ ከተማ የጀመረችው እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ችግሮቿን መለየትና ለዛ መስራት ይገባል ይላሉ፡፡ ስራ አጥ እየበዛ ባለበት በዚህ ወቅት ሀዋሳም የችግሩ ተጠቂ መሆኗን ታዝበዋል፡፡ ለመዝናናት ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
መጤ ባህሎች ከተማዋን እንዳይበክሉም ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ በመጠቆም፡፡ በመንግስት ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችም ቢሆን ችግር ያለባቸው እንደሆነ ታዝበዋል፡፡ እሳቸው በከተማው የማዘጋጃ ሹም ከነበሩበት ጊዜ ጋር በማነጻጸር አሁን ላይ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ችግር ያለባቸው በመሆኑ ሊቀረፍ ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ቢሮክራሲውን ፈጽሞ ማጥፋት ባይቻልም መቀነስ ግን ይቻላል፡፡ ከሙስና የጸዳ እና የተገልጋዮችን እርካታ መፍጠር ይገባል፡፡ ሀዋሳ አንጻራዊ ሰላም ያላት ከተማ እንደሆነች የሚካድ ባይሆንም ይህንንም ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡ ካላቸው የረጅም ጊዜ አገልግሎትና ልምድ አኳያም ለትውልዱም የምለው አለኝ ነው ያሉት፡፡ ያሁኑ ዘመን ወጣት በቴክኖሎጂ ተጽእኖ ውስጥ መውደቁን ታዝበዋል።
በርካታ ለሀገርና ለወገን የሚቆረቆሩ በስነ ምግባር የታነጹ እንዳሉ የማይካድ ቢሆንም የተወሰኑት ግን የስነ ምግባር ችግር ውስጥ ይገኛሉ ባይ ናቸው፡፡ ከብልሹ አሰራር የጸዳ ማህበረሰብ በመፍጠሩ ሂደት ወጣቶች ላይ መስራት ይገባል፡፡ በእሳቸው የማዘጋጃ ሹም በነበረሩበት ወቅት የከተማ ቦታ ለማግኘት የተወሳሰበ ችግር አልነበረም ይላሉ፡፡ ሹሙ ጋር ይቀርብና የተወሰኑ መሟላት የሚገባቸውን ነገር አሟልቶ ወደ ቴክኒክ ክፍል ይመራል፡፡ አካውንቱ ውስጥ የተወሰነ ገንዘብ አለያም በአይነት አሸዋ፣ ድንጋይ ማቅረቡም ይረጋገጥና ቦታው ይሰጠዋል፡፡ ለአንድ ሰው የሚፈቀደው አንድ ቤት ነው፡፡ 250 ካሬ ሜትር ተሰጥቶት ቤቱ በ70 ካሬ ሜትር እንዲያርፍ ይደረጋል። 32 ብር የማዕዘን ድንጋይ ከፍሎ ቦታውን ይረከባል፡፡ ካርታ ይሰጣል፡፡ ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚስተዋል ብልሹ አሰራር እንዳልነበረም ነው የሚገልጹት፡፡
የሀዋሳ እርሻ ልማት በቆሎ በ30 ብር ለነዋሪው ያቀርብ እንደነበርም አስታውሰዋል። የሀዋሳ ግብርና ኮሌጅም አትክልትና ፍራፍሪ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተትን ጨምሮ ለነዋሪው በቅናሽ ይቀርብ ነበር፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ስጋ በአራት ብር ለሽያጭ ያቀርብ ነበር። የዋጋ ቁጥጥር ነበር፡፡ እንዲያውም ይላሉ ባለታሪካችን ስጋ ከአራት ብር ከሃምሳ ወደ አምስት ብር በማስገባታቸው ለፍርድ ሸንጎ ቀርበው የተቀጡ ነጋዴዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡
በሳቸው ዘመን ባስገነቡት የህዝብ ዳቦ ቤት የአንድ ብር 10 ዳቦ ይሸጥ ነበር፡፡ ሙስና እንዳሁኑ የገነነበት ዘመን አልነበረም ይላሉ፡፡ በተለይ ከላይ ያሉ ሰዎች አካባቢ ሙስና የሚታሰብ እንዳልሆነ ነው ምስክርነታቸውን የሚሰጡት፡፡ እሳቸው የቁጥጥር ኮሚቴ አባል እንደነበሩ ያስታወሱት ሙስናንን መቆጣጠር ዋና ስራቸው ነበር፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው