‎የተገነባው የመስኖ ፕሮጀክት ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርናን በማስፋፋት የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አርሶ አደሮች ተናገሩ

‎የተገነባው የመስኖ ፕሮጀክት ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርናን በማስፋፋት የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አርሶ አደሮች ተናገሩ

በባስኬቶ ዞን ላስካ ዙሪያ ወረዳ ኦብጫ ጊንባ ቀበሌ የተገነባው የመስኖ ፕሮጀክት ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርናን በማስፋፋት የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የአካባቢው አርሶ አደሮች ገለጹ።

‎

‎የመስኖ ፕሮጀክቱ በክልሉ መንግሥት ድጋፍ በ77 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን ሙሉ በሙሉ የግንባታ ሥራው ተጠናቋል።

‎

‎የአካባቢው አርሶ አደሮች እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ በዝናብ ጥገኝነት ላይ ተመርኩዘው ያመርቱ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን የመስኖ ውሃውን በመጠቀም ወደ ምርት በመግባታቸው ከቀድሞው የተሻለ የምርት ዕድል ማግኘታቸውንና በዚህም መደሰታቸውን ተናግረዋል።

‎

‎በበጋ የመስኖ ወቅት በቆሎን ጨምሮ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቲማቲምና የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን እያመረቱ መሆኑን የጠቆሙት አርሶ አደሮቹ፣ በእርሻ ማሳዎቻቸው ላይ የተባይ ችግር በመኖሩ የማጥፊያ ኬሚካሎችና የባለሙያ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

‎

‎የቀበሌው የመስኖ ባለሙያ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ከ62 ሄክታር በላይ መሬትን የማልማት አቅም ያለው ሲሆን፣ ከ250 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል።

‎

‎በአንዳንድ የበቆሎና የአትክልት እርሻዎች ላይ የተባይ ምልክቶች መታየታቸውን ያረጋገጡት ባለሙያው፣ ችግሩን ለመቆጣጠር ከወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

‎

‎የኦብጫ ጊንባ ቀበሌ ሊቀመንበር በበኩላቸው፣ የመስኖ ውሃው ለሁሉም ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በፍትሐዊነት እንዲዳረስ ከቀበሌው ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት በየመንደሩ የውሃ አጠቃቀም ፈረቃ ተዘርግቶ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል።

‎‎የመስኖ ውሃ ማስተላለፊያ መሠረተ ልማቶች በደለል እንዳይዘጉ፣ በእንስሳትና በሌሎች ችግሮች እንዳይጎዱ በቀበሌው ምክር ቤት የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር መግባታቸውን አመልክተዋል።

‎

‎የላስካ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ቡቦ በበኩላቸው፤ በዙሪያ ወረዳው ከ2 ሺህ 600 በላይ ማሳዎችን በተለያዩ የአገዳ ሰብሎችና የጓሮ አትክልቶች በማልማት ከ580 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

‎

‎ከተያዘው ዕቅድ 250 ሄክታር መሬት በስንዴ የሚለማ መሆኑን የገለጹት አቶ ዳዊት፤ በተጠናቀቀው የኦብጫ ጊንባ መስኖ የተለያዩ ሰብሎችን ማልማት መቻሉን ጠቁመዋል።

‎

‎በተባይና በአረም ቁጥጥር ረገድ ቅድሚያ የማሳ ንጽህናን መጠበቅና ባህላዊ የመከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ተባዮችን ለመቆጣጠር የኬሚካል አቅርቦት መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

‎

‎በመስኖ አጠቃቀም ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍም ለግብርና ባለሙያዎችና ለአርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

‎

‎የባስኬቶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር በዛብህ ገበዬሁ በበኩላቸው፤ በዞኑ የሚገኙ ሁሉንም ውሃ ገብ ማሳዎች ለይቶ በባህላዊና በዘመናዊ የመስኖ አማራጮች ለማልማት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

‎

‎የዞኑን የውሃ ሀብት በልማት ሥራ በማዋል፣ የግብርና ምርትን ለማሳደግና የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማጠናከር በተያዘው አቅጣጫ መሠረት በዞኑ አምስት ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በመገንባት 319 ሄክታር መሬት እንደሚለማ ገልጸዋል።

‎

‎ከእነዚህ መካከል፣ በክልሉ መንግሥት ድጋፍ በ77 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የኦብጫ ጊንባ መስኖ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁንና የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።

‎

‎በዞኑ ጥገና የሚፈልጉ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በሕብረተሰቡ ተሳትፎና በመንግሥት ድጋፍ ለማስጠገን ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱንም ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን