“ቤሊንግሃም የዓለማችን ምርጡ አማካይ ተጫዋች ነው”ጆዜ ሞሪንሆ

“ቤሊንግሃም የዓለማችን ምርጡ አማካይ ተጫዋች ነው”ጆዜ ሞሪንሆ

የሪያል ማድሪዱ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ቡድናቸው በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አምስተኛ የምድብ ጨዋታ ፒኤስቪን ከመመራት ተነስቶ 5ለ1 ካሸነፈ በኋላ እንግሊዛዊውን አማካይ ጁድ ቤሊንግሃምን አድንቀዋል።

አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ቤሊንግሃም ሁሉም ነገር የተሟላለት ልዩ ተጫዋች መሆኑን ገልጸዋል።

አሰልጣኙ እንዳሉት “ቤሊንግሃም አካላዊ ጥንካሬ፣ ቴክኒክ፣ ታክቲካዊ የጨዋታ ግንዛቤ እና ከፍተኛ ፍላጎት አለው። ዛሬም ብቻውን ባይሆንም የጨዋታውን አቅጣጫ ቀይሮታል። ለእኔ ያለምንም ጥርጥር እሱ የዓለማችን ምርጡ አማካይ ነው“ በማለት ተናግረዋል።

አሰልጣኙ አክለውም “ እሱ በ10 ቁጥር፣ በ8 ቁጥር፣ በሁለት ወይም በአንድ የተከላካይ አማካይ ፊት መጫወት ይችላል። በባሎን ዶር ሽልማት ከምርጥ አስሩ ውስጥ አለመካተቱ እጅግ አስቆጪ ነው ያልኩትም ለዚህ ነው” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ሪያል ማድሪድ በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረውን ደካማ እንቅስቃሴ በሁለተኛው አጋማሽ እንዴት መቀየር እንደቻለ ሞሪንሆ ሲያስረዱ፣ የምስል መረጃዎችን መጠቀማቸው ወሳኝ እንደነበር ጠቁመዋል።

ከእረፍት መልስ ቤሊንግሃም ወደ ሜዳ መግባቱ እንዲሁም ቤርናርዶ ሲልቫ እና አርዳ ጉለር በመሃል ሜዳ ላይ መጣመራቸው ለቡድኑ አዲስ መነቃቃት እንደፈጠረ አሰልጣኙ ገልጸዋል።

“ፒኤስቪ በመጀመሪያው አጋማሽ አስቸግሮን ነበር፤ ኳስ ለመንጠቅም ተቸግረን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረነው ነበር። የፊት መስመር ተጫዋቾቻችን ሲነቁና በደስታ መጫወት ሲጀምሩ እንዲህ ያለው ውጤት ይመጣል” ሲሉ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ቡድናቸው ከመመራት ተነስቶ ቢያሸንፍም፣ ጨዋታዎችን በደካማ አቋም መጀመር አደገኛ መሆኑን ሞሪንሆ አሳስበዋል።

“ጨዋታዎችን በዚህ መልኩ የምንጀምር ከሆነ ገና ብዙ የምናስተካክለው ነገር አለ ማለት ነው። ቡድኔን ከመጀመሪያዋ ደቂቃ አንስቶ በተመሳሳይ ጥንካሬ እንዲጫወት ማድረግ ካልቻልኩ እኔ መፍታት ያለብኝ ችግር ነው። ከኋላ ተነስቶ ማሸነፍ ጥሩ ቢሆንም፣ በምንወስደው ስጋት ምክንያት ነገሮች ሊበላሹ ይችላሉ” በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በመጨረሻም ሞሪንሆ ስለ ቤሊንግሃም የመሪነት ባህሪ ሲናገሩ፣ ተጫዋቹ ለራሱ ያለው ከፍተኛ ግምት እና ጠንካራ የስራ ባህል ተፈጥሯዊ መሪ እንዳደረገው ገልጸዋል።

“ነገሮች ጥሩ በማይሄዱበት ጊዜ ብስጭቱን መደበቅ አይችልም፤ ነገር ግን ያንን ብስጭት በጠንካራ ስራ እና የቡድኑን ሞተር በማንቀሳቀስ ይታገለዋል። ጁድ ወደ ሜዳ ከገባ በኋላ የፊት መስመር ተጫዋቾቻችን ሙሉ በሙሉ በተለየ መንገድ መንቀሳቀስ ጀምረዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

በ2023 ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ሪያል ማድሪድን የተቀላቀለው ቤሊንግሀም በሎስብላንኮዎቹ ቤት 11ኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ጎሉን አስቆጥሯል።

በዚህም ለሪያል ማድሪድ ከተጫወቱት እንግሊዛዊያን ተጫዋች በነጩ ማልያ በሻምፒዮንስ ሊጉ ብዙ ጎሎችን ያስቆጠረ ቀዳሚው ተጫዋች ሆኗል።

ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ