በማንቸስተር ዩናይትድ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን ማልያ የተጫወቱ 7 ተጫዋቾች
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሊግ ፌዝ 5ኛ ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት ማንቸስተር ዩናይትድ ከሜዳው ውጪ ከፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር የሚያደርገውን ወሳኝ ጨዋታ ተከትሎ፣ በሁለቱም ታላላቅ ክለቦች ታሪክ ውስጥ አሻራቸውን ያኖሩ ሰባት ተጫዋቾች ዝርዝር ትኩረትን ስቧል።
በተለይም የወቅቱ የዩናይትድ አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ የቀድሞ ክለቡን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገጥምበት መሆኑ ጨዋታውን ይበልጥ ተጠባቂ አድርጎታል።
በሁለቱ ክለቦች መካከል የነበረውን የዝውውር እና የታሪክ ትስስር ከሚያሳዩት 7 ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደሙ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነው።
የአምስት ጊዜ የባሎንዲኦር አሸናፊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከስፖርቲንግ ሊዝበን አካዳሚ ወጥቶ በፈረንጆቹ 2003 ወደ ኦልድትራፎርድ በመዘዋወር የዓለማችን ኮከብ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።
ሌላኛው ተጠቃሽ ተጫዋች ሉዊስ ናኒ ሲሆን ልክ እንደ ሮናልዶ ከስፖርቲንግ ሊዝበን ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ በመምጣት ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል። በጆዜ አልቫላዴ ስታዲየም በሶስት የተለያዩ አጋጣሚዎች ለስፖርቲንግ ተጫውቷል።
ከሁለቱ ተጫዋች በመቀጠል የወቅቱ የማንቸስተር ዩናይት አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ ይጠቀሳል።
የስፖርቲንግ ሊዝበን ቁልፍ ተጫዋች እና አምበል የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ የማንቸስተር ዩናይትድ አምበል በመሆን የቀድሞ ክለቡን ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ምሽት ይገጥማል።
ኡሯጓይው አማካይ ማኑኤል ኡጋርቴ በአሁኑ ወቅት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ቢርቅም፣ የዩናይትዱ አማካይ ከዚህ ቀደም የስፖርቲንግ ሊዝበን ማልያን ለብሶ ተጫውቷል።
እንዲሁም እንግሊዛዊው ግብ ጠባቂ ፒተር ሽማይክል እ.ኤ.አ በ1999 ማንቸስተር ዩናይትድ የሶስትዮሽ ዋንጫ (Treble) እንዲያነሳ ካገዘ በኋላ ኦልድትራፎርድን ለቆ ቀጣይ መዳረሻውን ስፖርቲንግ ሊዝበን አድርጎ ነበር።
በአርሰናል ቤት የሚኬል አርቴታ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ የሚገኘው ጋብሪኤል ሄንዜ፣ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስር ለማንቸስተር ዩናይትድ ከመፈረሙ አስቀድሞ፣ በፈረንጆቹ 1998 ከቫላዶሊድ በውሰት ለስፖርቲንግ ሊዝበን ተጫውቷል።
ሌላኛው አርጀንቲናዊው ተከላካይ ማርኮስ ሮሆ ከስፖርቲንግ ወደ ዩናይትድ ሲዘዋወር፣ ናኒ በተቃራኒው አቅጣጫ በውሰት ወደ ስፖርቲንግ እንዲያመራ በተደረገ ስምምነት ውስጥ ተካትቶ ለማንቸስተር ዩናይትድ ተጫውቶ ያሳለፈ ተጫዋች ነው።
ይህ የሰባቱ ተጫዋቾች የጋራ ታሪክ፣ በሁለቱ ክለቦች መካከል ለዓመታት የዘለቀውን ጠንካራ የእግር ኳስ ግንኙነት በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
በማንቸስተር ዩናይትድ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን ማልያ የተጫወቱ 7 ተጫዋቾች
“ቤሊንግሃም የዓለማችን ምርጡ አማካይ ተጫዋች ነው”ጆዜ ሞሪንሆ
“አርሰናል ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ተጨማሪ ዕድል እና የተሻለ አጨራረስ ያስፈልገዋል” ሚኬል አርቴታ