ፕሮጀክት የማኅበረሰቡን ኑሮ መለወጥ የሚያስችሉ ችግር ፈቺ ተግባራትን እያከናወነ ነው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ

ፕሮጀክት የማኅበረሰቡን ኑሮ መለወጥ የሚያስችሉ ችግር ፈቺ ተግባራትን እያከናወነ ነው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ

ፎሉር ኢትዮጵያ ፕሮጀክት የማኅበረሰቡን ኑሮ መለወጥ የሚያስችሉ ችግር ፈቺ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

‎

‎በጌዴኦ ዞን በምርት ዘመኑ ፕሮጀክቱ ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ የመስክ ምልከታ እና የአርሶ አደሮች የልምድ ልውውጥ መርሀግብር ተካሂዷል።

‎

የተከናወኑትን ተግባራት የጎበኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ  በቡና ችግኝ ዝግጅት፣ አፈርና ውሃ ጥበቃ ዘርፍ አበረታች ተግባር አከናውኗል።

‎

‎የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትና እንዲሁም ማህበራትን በማደራጀት ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረገበት መንገድ ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሰሩም  አስረድተዋል።

‎

‎የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ በድሉ አየለ እንደገለጹት፤ የዞኑ መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ከሚያደርገው ርብርብ በተጓዳኝ ፕሮጀክቱ እያከናወነ ያለው ተግባር ምርታማነትን በማሻሻል አይተኬ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

‎

‎በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ፎሉር-ኢትዮጵያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አለምበጁ ክፍሌ፤ ፕሮጀክቱ  በተቀናጀ የመሬት አያያዝ ዙሪያ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ አዘጋጅቶ በዘርፉ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ አመላካች አቅጣጫ በማስቀመጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል።

‎

‎በበጀት አመቱ ከ340 ሄክታር በላይ ያረጁ የቡና ዛፎችን ነቅሎ በመትከልና በመጎንደል የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ መስራት መቻሉን ገልፀው፤ የተከናወኑትን ተግባራት አርሶአደሮች የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ማድረጋቸውን አስገንዝበዋል።

‎

‎ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል አርሶአደር አስካለች ታዬ እና መለሠ ዘነበ በሰጡት አስተያየት ከጉብኝታቸው ጠቃሚ ግብዓት ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ ያዩትን በማሳቸው ለመተግበበር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

‎

‎ዘጋቢ፡ አማኑኤል ትዕግሥቱ – ከይርጋጨፈ ጣቢያችን