የቀኑ መከበር ህብረ ብሄራዊ አንድነትና እኩልነትን በማረጋገጥ ጠንካራ ሀገር በመገንባት ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አስታወቀ
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል መከበር ብሔር ብሔረሰቦች ህብረ ብሄራዊ አንድነታቸውንና እኩልነታቸውን በማረጋገጥ ጠንካራ ሀገር በመገንባት ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አስታውቋል።
21ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ ከመንግስት ሰራተኛው ጋር የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንደተናገሩት፤ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በህዝቦች መካከል መከባበርን፣ መቻቻልን እና ሊጠቅሙ የሚችሉ ዕሴቶችን አንዱ ከአንዱ የሚቀስምበት መሆኑን በመረዳት ልናከብር ይገባል።
የብሔር፣ ብሔረሰቦች ቀን በዓል የብሔር፣ ብሔረሰቦች መብት፣ እኩልነት፣ አንድነትና አብሮነትን የሚያሳድግ እንዲሁም ለሀገራዊ መግባባትና ለሀገረ መንግስት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
21ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል በኦሮምያ ክልል ጅማ ከተማ “በብዝሃነት የደመቀች፤ በምክክር የጸናች ስልጡን ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን በዓሉን ለማክበር የሚያልፉ እንግዶችን የአካባቢውን ባህልና እሴት በማስተዋወቅ እንግዳ ተቀባይነታችንን ማሳየት ይጠበቅብናል ብለዋል።
አቶ አበራ አክለውም በመንግስት ተቋማት የሚሰሩ አገልጋዮች ብሔር ብሔረሰቦች ያላቸውን ልዩነቶች እንደ ውበትና የጋራ ሀብት በመመልከት፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይትና በምክክር የመፍታት ባህልን በማጎልበት የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሀሰን ናስር በበኩላቸው፤ ህዳር 29 የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ሀገራችን የምትተዳደርበትን ሕገ መንግስት ያፀደቀችበት ቀን በመሆኑ ሀገራችን ለብሔር፣ ብሔረሰቦች የሰጠችውን ትኩረት የሚያመላክትም ነው ብለዋል።
የበዓሉ መከበር ብሔር ብሔረሰቦች ህብረ ብሄራዊ አንድነታቸውንና እኩልነታቸውን በማረጋገጥ ጠንካራ ሀገር በመገንባት ረገድ ፋይዳው የጎላ ስለመሆኑም ኃላፊው አስረድተዋል።
ዕለቱን በማስመልከት የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የዞኑ ፍትህ መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ግሩም ገብሩ እንዳነሱት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ያሏት ሀገር በመሆኗ አንዱ የሌላውን ባህል፤ ቋንቋና እሴት ለመጠበቅ ቀኑን ማክበር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ብሔር ብሔረሰቦች ህብረ ብሔራዊ አንድነታቸውና የወንድማማችነት እሴቶቻቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት ከቻሉ ለሀገር እድገት ዋነኛ መሳሪያ መሆን እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነትና በእኩልነት መኖር ከቻሉ ውብ ባህሎቻቸውን ለሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ለማስተዋወቅና ለማሳየት እንደሚጠቅም አስረድተዋል።
በዓሉ ወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር የብሔር፣ ብሔረሰቦችን ብዝሃነትን ማክበር፣ መከባበርና በመግባባት አብሮ መኖርን ማጠናከር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ዳዊት ዳበራ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
ፕሮጀክት የማኅበረሰቡን ኑሮ መለወጥ የሚያስችሉ ችግር ፈቺ ተግባራትን እያከናወነ ነው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ
ሰራተኞች እና አሰልጣኞች በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩና ውጤታማ የስራ ቦታ ተግባቦት እንዲኖራቸው በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ
የተገነባው የመስኖ ፕሮጀክት ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርናን በማስፋፋት የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አርሶ አደሮች ተናገሩ