ሰራተኞች እና አሰልጣኞች በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩና ውጤታማ የስራ ቦታ ተግባቦት እንዲኖራቸው በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ
የኢትዮጵያ የቴክኒክ ልህቀት ኢንስቲትዩት ሀዋሳ ካምፓስ ከኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለተቋሙ ሠራተኞች የህይወት ክህሎት ሥልጠና ሰጠ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ የሥራ ፈጠራ ባህልን ለማሳደግና ሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ የተቋቋመ፣ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ስር የሚገኝ መንግሥታዊ የሆነ ተቋም ነው።
ተቋሙ ዓለም አቀፍ የስራ ፈጠራ ሳምንት በማስመልከት ከኢትዮጵያ የቴክኒክ ልህቀት ኢንስቲትዩት ሀዋሳ ካምፓስ ጋር በመተባበር የህይወት ክህሎት ሥልጠና ለተቋሙ ስራተኞች ሰጥቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት አሰልጣኝና የንግድ ማማከር አገልግሎት ባለሙያ አቶ ፀጋ ሳሙኤል የሠራተኞችን የሥራ ተነሳሽነት፣ የእርስ በርስ ተግባቦት እና ችግር የመፍታት አቅም ለማሳደግ እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ያለመ የአንድ ቀን ስልጠና መሆኑን ተናግረዋል።
በተቋማት ደረጃ የሚስተዋሉ አለመግባባቶችና የባህሪይ ግድፈቶች የተገልጋዩን ማህበረሰብ ስብዕና የሚነኩ የስነ-ምግባር ጥሰቶች መኖራቸውን ገልፀዋል። ይህንን ለማረምና የተቋማት አገልግሎት ይበልጥ ለማሳደግ እንደ ሀገር የኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት የህይወት ክህሎት ስልጠና በመስጠት በትኩረት እየሰራ እንደሆነ አቶ ፀጋ ሳሙኤል አክለው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የቴክኒክ ልህቀት ኢንስቲትዩት ሀዋሳ ካምፓስ ተወካይ አቶ ተገኝ መሐድም እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶች፣ በብረታ ብረትና ብየዳ፣ በቀርከሃና በሌሎችም ዘርፎች በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። ይህን የህይወት ክህሎት ስልጠና ለተቋሙ ከፍታና በሙያው የሚያገለግሉ የተቋሙ ሰራተኞች አጋዥ መሆኑን አንስተዋል።
በሥልጠናው የተሳተፉት የኢትዮጵያ የቴክኒክ ልህቀት ኢንስቲትዩት ሀዋሳ ካምፓስ ሠራተኞች የህይወት ክህሎት ሥልጠናው የጊዜ አጠቃቀምን በተገቢው እንዲያውሉ ለዕለት ተዕለት ሥራቸው እጅግ አጋዥ እንደሚያደርግላቸው ገልጸዋል።
መልካም የሥራ ሥነ-ምግባርን የተላበሰና የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚረዳ ጠቃሚ እውቀት የቀሰሙበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የቴክኒክ ልህቀት ኢንስቲትዩት ሀዋሳ ካምፓስ የሰው ኃይል ልማትን በማጠናከር በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቁ የቴክኒክ ባለሙያዎችን የማፍራት ተልዕኮውን እየተወጣ እንደሆነ ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፡ ጠቅልል ቀድሩ

More Stories
የቀኑ መከበር ህብረ ብሄራዊ አንድነትና እኩልነትን በማረጋገጥ ጠንካራ ሀገር በመገንባት ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አስታወቀ
ፕሮጀክት የማኅበረሰቡን ኑሮ መለወጥ የሚያስችሉ ችግር ፈቺ ተግባራትን እያከናወነ ነው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ
የተገነባው የመስኖ ፕሮጀክት ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርናን በማስፋፋት የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አርሶ አደሮች ተናገሩ