የመሬት ሀብትን በተቀመጠለት ህግና ደንብ በማስተዳደር ከዘርፉ በሚገኘው ገቢ የከተሞችን የመሠረተ ልማት ዕድገት ለማፋጠን መሥራት ይገባል – የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

የመሬት ሀብትን በተቀመጠለት ህግና ደንብ በማስተዳደር ከዘርፉ በሚገኘው ገቢ የከተሞችን የመሠረተ ልማት ዕድገት ለማፋጠን መሥራት ይገባል – የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

የመሬት ሀብትን በተቀመጠለት ህግና ደንብ በማስተዳደር ከዘርፉ በሚገኘው ገቢ የከተሞችን የመሠረተ ልማት ዕድገት ለማፋጠን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ ባህሩ ገለጹ።

በጎፋ ዞን የመሬት አስተዳደርና የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያዎች የ2018 ዓ.ም አፈጻጸምና የ2019 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምና ቀጣይ ዕቅድ ዙሪያ የጋራ ምክክር አካሂደዋል።

የጎፋ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ያዕቆብ ደበላ በምክክሩ እንደገለጹት፤ ለከተሞች ዘላቂ ዕድገት የገቢ አቅም ወሳኝ በመሆኑ ከመሬትና ከሌሎች ምንጮች የሚገኘውን ገቢ በሙሉ በሕጋዊ አግባብ መሰብሰብ ይገባል።

የዞኑ ከተሞች ቁጥርና የአስተዳደር አቅም እያደገ መምጣቱን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ቀደም ሲል አንድ የከተማ አስተዳደር ብቻ ከነበረበት አሁን ራሳቸውን የቻሉ አስተዳደሮችን ጨምሮ ወደ 35 ከተሞች መድረሱን አብራርተዋል።

የጎፋ ዞን መሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ኢንጂነር ተስፋሁን ጉሌ በበኩላቸው፤ በሁሉም ከተሞች በሕገወጥ መንገድ የተያዙ መሬቶችን በሕጋዊ አግባብ ማስተካከል፣ የመሬት መረጃ አያያዝን ማዘመንና ተገቢ ያልሆነ የመሬት አጠቃቀምን መከላከል በትኩረት የሚሠሩ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የመሬት ሀብትን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር አርሶአደሩ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመው፤ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለማኅበራዊ ትስስርና ለተፈጥሮ ሚዛን መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ ባህሩ በበኩላቸው፤ የመሬት ሀብትን በተቀመጠለት ሕግና ደንብ በማስተዳደር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለከተሞች መሠረተ ልማት ዕድገት ማዋል እንደሚገባ ገልጸዋል።

መሬት አስተዳደር ከዚህ ቀደም በማዘጋጃ ቤት ሥር የነበረ ቢሆንም ራሱን ችሎ ከተደራጀ በኋላም በሁለቱ ተቋማት መካከል የሚታዩ የአሠራር ችግሮችን ሙሉ በሙሉ በመፍታት የተቀናጀ አፈጻጸም ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አያይዘውም በከተሞች የኮሪደር ልማት ዙሪያ ያሉ የግንዛቤ ክፍተቶችን በማረም በልማቱ የሚካተቱ ሰፋፊ ተግባራትን በማቀናጀት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በመድረኩ የሁለቱ መምሪያዎች የ2018 ዓ.ም አፈጻጸምና የ2019 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርቶችና ቀጣይ ዕቅዶች ቀርበው ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን