የኢትዮጵያ ፀጋዎች
ምድረ ቀደምት ተብላ የምትጠራው ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተቸረች ድንቅ ምድር ናት፡፡ የማይነጥፍ ጸጋ ባለቤትም ነች፡፡ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶቿ ዘመናትን የተሻገሩ ናቸው፡፡ ለዚህም በዓለማችን ላይ በርካታ ቅርሶች ካላቸው ሀገራት ተርታ ተሰልፋለች፡፡
ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ብቻ ሳይሆን ለዘመናት የዘለቁ ባህላዊ እሴቶችም ባለቤት ነች፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ማንቷን ለዓለም ማህበረሰብ ያስተዋወቁ ድንቅ ባህሎችና እሴቶችን ተጎጽፋለች፡፡
ከዚሁ መነሻ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ)፣ ኢትዮጵያ የተጎናጸፈቻቸውን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶቿን እንዲሁም በማህበራዊ ሕይወት ጎልተው የወጡ ባህላዊ እና ኃይማኖታዊ እሴቶችን በሚዳሰሱና በማይሰሱ ቅርስነት አስፍሯቸው ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህ ቅርሶች መካከል በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና በሲዳማ ክልሎች የሚገኙና በዩኔስኮ የተመዘገቡትን በጥቂቱ እንመልከት፡፡
የታችኛው የኦሞ ሸለቆ (Lower Valley of the Omo)
የታችኛው የኦሞ ሸለቆ በደቡባዊ ኢትዮጵያ ክፍል ከቱርካና ሐይቅ አጠገብ የሚገኝ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ታሪካዊና ባህላዊ ቦታ ነው፡፡ በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከኬኒያ እና ደቡብ ሱዳን ድንበር አቅራቢም ይገኛል፡፡ አጠቃላይ እስከ 165 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት አለው፡፡
አካባቢው የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ የሚጠናበት እና ከ1 እስከ 3.5 ሚሊየን ዓመታት ያስቆጠሩ የጥንታዊ እንስሳትና የሰዎች ቅሪተ አካላት (Hominid fossils) እንዲሁም የድንጋይ መሣሪያዎች እንደ ተገኙበት የዩኔስኮ መረጃ ያመለክታል፡፡
እስከ 195 ሺህ ዓመታት ያስቆጠሩ ቀደምት የሆሞ ሳፒየንስ (የዘመናዊ ሰው) አጥንት ፍርስራሾች ተገኝተዋል። አካባቢው በ1980 ዓ.ም. በዩኔስኮ በሚዳሰስ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ ምድር (Konso Cultural Landscape)
በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኝና በ2003 ዓ.ም በዩኔስኮ በሚዳሰስ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ታሪካዊና ባህላዊ ስፍራ ነው። ይህ ቅርስ የኮንሶ ማህበረሰብ ከ400 ዓመታት (21 ትውልዶች) በላይ ደረቅና ገደላማ መሬትን በባህላዊ እውቀት አልምቶ ለኑሮ ምቹ ያደረገበትን ጥበብ እንደሚሳይ ዩኔስኮ በድረገጹ ያሰፈረው መረጃ ያመለክታል።
የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ ምድር በተለያዩ አስደናቂ የምህንድስና እና ባህላዊ እሴቶች የታጀበ ነው። ስፍራው ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 540 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ ይገኛል። የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና የዝናብ ውሃን ለመያዝ እስከ 5 ሜትር ከፍታ ባላቸው የድንጋይ ግድግዳዎች የተገነቡ የእርሻ እርከኖች የመልክዓ ምድሩ መገለጫዎች ናቸው፡፡
በድንጋይ ግንብ የታጠሩት መንደሮቹ (ፓሌታ/ Paletas) ለመከላከያ እንዲመቹ በኮረብታዎች ላይ የተቆረቆሩና ከአንድ እስከ ስድስት ተደራራቢ የድንጋይ አጥር ያላቸው ጥንታዊ መንደሮች ናቸው።
የማህበረሰብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ወይም “ሞራ” (Mora) ተብለው የሚጠሩት በመንደሮቹ መሃል የሚገኙ ባህላዊ አደባባዮች ሲሆኑ የማህበራዊ፣ የባህልና የፍትህ ስርዓቶች የሚከወኑባቸው ስፍራዎች ናቸው።
የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር (Gedeo Cultural Landscape)
የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጌዴኦ ዞን የሚገኝ ነው፡፡ መልክዓ ምድሩ በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም በዩኔስኮ በሚዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቧል። ከኢትዮጵያ 10ኛው፣ ከአፍሪካ ደግሞ 100ኛው የዓለም ቅርስ ሆኖ ነው የተመዘገበው።
መልክዓ ምድሩ በምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ጠርዝ ላይ 29 ሺህ 620 ሄክታር ስፋት ያለውን ቦታ ይሸፍናል። የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ እና ተፈጥሮን ሳይጎዳ ለሺህ ዓመታት እንዴት መኖር እንደሚችል የሚያሳይ ሕያው ምሳሌ ነው።
መልክዓ ምድሩ ላይ ከሚገኙት መካከል ጥንታዊ ተክል ድንጋዮች ሲጠቀሱ ከ6 ሺህ በላይ ጥንታዊያን የቆሙ ድንጋዮች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተለይም የቱቶ ፈላ እና የጨልባ ቱቲቲ ትክል ድንጋዮች የአካባቢውን የጥንት ሥልጣኔ እና የቀብር ሥርዓት ታሪክ የሚመላክቱ ናቸው።
ሌላው ባህላዊ የጥምር ግብርና ሥርዓት ተጠቃሽ ሲሆን የጌዴኦ ሕዝብ ትላልቅ ሀገር በቀል ዛፎችን ሳይቆርጥ በጥላቸው ስር እንሰት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆነውን የይርጋጨፌ ቡና እና የተለያዩ የስራስር ሰብሎችን በደረጃ ያለማል። ይህ ዘዴ የአፈር መሸርሸርን የሚከላከልና ብዝሃ ሕይወትን የሚጠብቅ ነው።
የጢያ ትክል ድንጋዮች (Tiya Archaeological Site)
ይህ ጥንታዊ የአርኪኦሎጂ ቦታ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን፣ ሶዶ ወረዳ ውስጥ ይገኛል። ቅርሱ በአውሮፓዊኑ 1980 በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቧል።
እንደ ዩኔስኮ መረጃ 36 ጥንታዊ ትክል ድንጋዮች የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 32ቱ በተለያዩ እንቆቅልሽ ምልክቶችና ቅርጾች (በተለይም የጎራዴ ምስሎች) የተቀረጹ ናቸው።
ትክል ድንጋዮቹ ከ10ኛው እስከ 15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ የቆሙ ጥንታዊ የመቃብር ምልክቶች እንደሆኑ የአርኪኦሎጂ ጥናቶች ያመለክታሉ።
የካፋ ብዝኃ ሕይወት ጥብቅ ክልል (Kaffa Biosphere Reserve)
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በካፋ ዞን የሚገኝ እና የዓለም ታዋቂው የአረቢካ ቡና መገኛ በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኘ የተፈጥሮ ጥብቅ ስፍራ ነው።
ይህ ስፍራ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምዕራብ 460 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በአውሮፓዊያኑ ሰኔ 2010 በዩኔስኮ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የባዮስፌር ጥብቅ ክልል ሆኖ መመዝገቡን የተቋሙ መረጃ ያመለክታል።
ከ760 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሸፍን ሲሆን ከኢትዮጵያ ቀሪ የተራራማ ጥብቅ ደኖች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ይይዛል። ጥቅጥቅ ያሉ የዝናብ ደኖች፣ የቀርከሃ ደኖች፣ ረግረጋማ ቦታዎችና የወንዝ ተፋሰሶች ይገኙበታል።
በዓለም ላይ በስፋት የሚጠጣው የአረቢካ ቡና ዋና መገኛና የዘረመል (Genetic diversity) ማዕከልም ነው፡፡ ወደ 5 ሺህ የሚጠጉ የዱር ቡና ዝርያዎች በዚህ ደን ውስጥ ይገኛሉ።
በዚሁ ስፍራ የዱር እንስሳትና የዕፅዋት ሀብት በብዛት ሲገኝ፤ እንደ አንበሳ፣ ነብርና ጉሬዛ ያሉ 300 የሚጠጉ የአጥቢ እንስሳት ዝርያዎች፣ 178 የአዕዋፍ ዝርያዎች እንዲሁም 244 የዕፅዋት ዝርያዎች ተመዝግበዋል።
የሸካ ደን ብዝኃ ሕይወት ጥብቅ ክልል (Sheka Forest Biosphere Reserve)
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፣ በሸካ ዞን ውስጥ (በማሻ፣ አንደራቻ እና የኪ ወረዳዎች) ይገኛል። ከከፍተኛ ደጋማ ተራሮች እስከ ሞቃታማ ቆላማ አካባቢዎች የሚዘልቅ ልዩ ሥነ-ምህዳር አለው።
እ.ኤ.አ. በ2012 የዓለም ብዝኃ ሕይወት ጥብቅ ክልል (Biosphere Reserve) ሆኖ በዩኔስኮ የተመዘገበም ታላቅ የተፈጥሮ ሀብት ነው። ደኑ በአጠቃላይ 238 ሺህ 750 ሄክታር ስፋት ያለው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ከቀሩት ጥቂት ጥቅጥቅ ያሉ የዝናብ ደኖች አንዱ መሆኑን የዩኔስኮ መረጃ ያመለክታል።
በደኑ ውስጥ ከ300 በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 55ቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ (ብርቅዬ) ናቸው። ሰፋፊ የቀርከሃ ደኖች እና ዕድሜ ጠገብ ሀገር በቀል ዛፎች የደኑ ዋና መገለጫዎች ናቸው።
ደኑ ከ50 በላይ አጥቢ የዱር እንስሳት ዝርያዎች፣ ከ200 በላይ የአእዋፍ ዝርያዎች (10 ብርቅዬ የሆኑ) እና 20 የአምፊቢያን ዝርያዎች መኖሪያ ነው። እንደ አንበሳ፣ ነብር፣ ጎሽ እና የተለያዩ የዝንጀሮ ዝርያዎች ያሉ 38 በመጥፋት ላይ ያሉ የዱር እንስሳት በዚህ ክልል ይገኛሉ።
የፊቼ ጫምባላላ በዓል
የፊቼ ጫምባላላ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡ ከ1 ሺህ 800 ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሲዳማ ብሔር ዘንድ ፊቼ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ሲሆን፣ ቤተሰቦችና ጎረቤቶች ተሰባስበው “ቡርሳሜ” (ከእንሰት እና ከወተት የሚዘጋጅ) ምግብ የሚበላበት ዕለት ነው።
ጫምባላላ ደግሞ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ቀን ሲሆን፤ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የይቅርታ መገለጫ ነው። በዓሉ የሚውልበት ትክክለኛ ቀን በሲዳማ አያንቱዎች (የከዋክብትና የጨረቃ ዑደት አዋቂዎች) ጥቆማና ስሌት ይወሰናል።
በበዓሉ ወቅት የቀድሞ ቂምና ቁርሾ ይጠፋል፤ የተጣሉ ይታረቃሉ፣ ተሰዳጆች ይመለሳሉ። በተጨማሪም በሙዚቃ፣ በጭፈራ (ቄጠላና ኛፋሮ) እንዲሁም ሁሉቃ (ከሸምበቆ ወይም ከቅጠል የሚሰራ መተላለፊያ) በማቆም በዓሉ ይከበራል።
የፊቼ ጫምባላላ በዓል ኅዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በዓለም የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ተመዝግቧል።
የጊፋታ በዓል
ጊፋታ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ብሔር የሚከበር ታላቅ የዘመን መለወጫ በዓል ነው። “ጊፋታ” ማለት መጀመሪያ ወይም መነሻ ማለት ሲሆን ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያሻግር እንደ ድልድይ ይቆጠራል።
ጊፋታ በየዓመቱ በመስከረም ወር (በተለይ ከመስከረም 8 እስከ 14 ወይም ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት መባቻ ባሉት ቀናት) ይከበራል።
በጊፋታ ወቅት፣ ወላይታዎች ይጨፍራሉ እና በባህላዊ ምግቦች ይደሰታሉ። የጊፋታ ፋይዳ ያለፉትን ጉዳዮች ማስወገድ እና እንደገና መጀመር፣ ያለፉትን አለመግባባቶች ማስታረቅ እና የቤተሰብ እና የማህበረሰብ ግንኙነቶችን ማጠናከር ነው።
የወላይታ ሕዝብ የዘመን መለወጫ ጊፋታ በአውሮፓዊያኑ ታኅሣስ ወር 2025 በዩኔስኮ የዓለም የማይዳሰስ የባህል ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል።
ዘጋቢ፡ ኢያሱ ታዴዎስ

More Stories
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ
የመሬት ኩታ ገጠም የአስተራረስ ስርአትን በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንና ምርታማነትን ማሳደግ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ገለፁ
አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በመሰብሰብ ሊከሰት የሚችለውን የምርት ብክነት መከላከል እንዳለበት ተገለፀ