ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የቤተሰብ አቅም በመጠቀም እየተሰበሰበ መሆኑ ተገለፀ

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የቤተሰብ አቅም በመጠቀም እየተሰበሰበ መሆኑ ተገለፀ

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የቤተሰብ አቅም በመጠቀም እየሰበሰቡ መሆናቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀቤና ልዩ ወረዳ ያነጋገርናቸዉ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በልዩ ወረዳው በበልግና በመኽር እርሻ በዘር ከተሸፈነው 29 ሺህ ሄክታር ሰብል የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የልዩ ወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ገልጿል።

በተለያዩ አከባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመጣሉ ምክንያት የምርት ብክነት እንዳይከሰት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

በልዩ ወረዳው ምርት ሲሰበስቡ አግኝተን ካነጋገርናቸዉ አርሶአደሮች መካከል የዘቢሞላ ቀበሌ ነዋሪ የሆነውን አርሶአደር ተገኝ አስፋው ጨምሮ የፈረጀቴ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር መሀመድ ሞሳ እና አክመል ሁሴን እንደተናገሩት፤ በተያዘዉ የበልግና የመኽር እርሻ እያንዳንዳቸዉ ከሁለት ሄክታር በላይ ማሳ በበቆሎና በጤፍ ሰብል መሸፈናቸውን አስታውሰው፤ በአሁን ወቅት ምርት የማሰባሰብ ተግባር ላይ መሆናቸዉን ገልጸዋል።

በበልግ ወቅት በዘር የተሸፈነውን የበቆሎ ሰብል በመሰብሰብ ማሳቸውን በሽንብራ መሸፈናቸውን ያነሱት አርሶ አደሮቹ፤ አሁን ላይ እየጣለ ያለው ዝናብ ምንም እንኳን ለሽንብራ ሰብል አስፈላጊ ቢሆንም በሌሎች በደረሱ እና ለመሰብሰብ ዝግጁ በሆኑ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ አመላክተዋል።

በመሆኑም የቤተሰብ አባላት የስራ አቅም በማስተባበር የደረሱ ሰብሎችን በጥራትና በፍጥነት እየሰበሰቡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በልዩ ወረዳዉ የዘቢሞላ ቀበሌ የግብርና ባለሙያ የሆኑት አቶ አብድልጀሊል ሸምሱ እንዳሉት፤ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም አርሶአደሩ የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት እንዲያነሳ እየተደረገ ነው።

በቀበሌው በበልግ እርሻ በሰብል ከተሸፈነ 650 ሄክታር የበቆሎ ሰብል ሙሉ በሙሉ መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመው፤ በመኽር እርሻ በዘር ከተሸፈነዉ 365 ሄክታር ጤፍ ከ214 ሄክታር በላይ የሚሆነውን መሰብሰብ መቻሉንና ቀሪዉን በሚቀጥሉት ቀናት ተሰብስቦ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድል ሽኩር ደሊል እንዳሉት፤ በ2018/19 የምርት ዘመን በበልግ እና በመኸር እርሻ የለማ 29 ሺህ ሄክታር መሬት ምርት የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

በምርት ዘመኑ በበልግ ወቅት የለማ 16 ሺህ 500 የኩታ ገጠም የበቆሎ ሰብል ሙሉ በሙሉ መሰብሰብ መቻሉን ያነሱት ምክትል አስተዳዳሪው፤ አሁን ላይ በመኸር ወቅት የለማ የጤፍ ሰብል የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑንና ሂደቱ ከግማሽ በላይ መድረሱንም አንስተዋል።

የምርት አሰባሰቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ እንደ ልዩ ወረዳ 1 ነጥብ 85 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አቶ አብድል ሽኩር ደሊል ገልፀው፤ አርሶአደሩ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የምርት ብክነት እንዳይከሰት በፍጥነት መሰብሰብ እንዳለበት አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን