የትምህርት ጥራት ችግሮችን በተገቢው መንገድ ለመቅረፍና በዘርፉ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ሁሉም በቅንጅት መሥራት እንዳለበት ተጠቆመ


‎
‎በጌዴኦ ዞን ‌የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት በ2018 ትምህርት አፈጻጻም እና በ2019 1ኛ ሩብ ዓመት የትምህርት ሥራዎች አፈጻጻም ግምገማ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
‎
‎የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መብራቱ ኦብሴ መድረኩን በንግግር በከፈቱበት ወቅት፣ በአሁኑ ወቅትት በክልል ደረጃ የትምህርት አመራሮች ሪፎርም ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን አንስተው፤ እንደ አገር የገጠመንን የትምህርት ስብራት ለመጠገንም ሁሉም ባለድርሻ  አካላት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚገባቸው አስረድተዋል።
‎
‎በመልካም ስብዕና የተቀረጹ ዜጎችን ለማፍራት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል ያሉት ኃላፊው፣ ለመማር ማስተማር ሥራ ተግባራዊነት የግብአት አቅርቦት ማሟላትና መምህራንም የዓመቱን የመማር ማስተማር ሥራቸውን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በማጠናቀቅ  የታሰበውን ውጤት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
‎
‎የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ መንግሥቱ ተክሌ ባስተላለፉት መልዕክት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመረባረብ ጥሩ ውጤት ለማምጣት መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ በዚህም የከተማ አስተዳደሩና ትምህርት ጽ/ቤቱ በጋራ በመቀናጀት ለውጤቱ መመዝገብ እንደሚሠሩ አመላክተዋል።
‎
‎የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክብረወሰን ተፈራ በበኩላቸው ለመማር ማስተማሩ ሂደት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ካልተቻለ የሚጠበቀውን ውጤት ማስመዝገብ እንደማይቻል አስታውሰው፤ መንግሥት ለትምህርት ከሰጠው ትኩረት በተጨማሪ ሁሉም ባለድርሻዎች አሻራቸውን ማሳረፍ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
‎
‎‌እንደ አገር እየተተገበረ ካለው አራት የኢንሼቲቭ ሥራዎች አንፃር ትምህርት ለትውልድ፣ የተማሪ ምገባ፣ ሞዴል ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት ግንባታ እና የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ ልዩ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው፤ ቀደም ሲል የተፈጠረውን የትምህርት ስብራት ታሪክ በውጤት መቀየር እንደሚገባ አሳስበዋል።
‎
‎የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት ማጎልበት፣ የመምህራንን ሙያዊ ብቃት ማሳደግና ወላጆች በልጆቻቸው ትምህርት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማበረታታት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ወሳኝነት ስለሚኖረው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊዎች ናቸው።
‎
‎በመድረኩ የከተማ አስተዳደር ከንቲባው አቶ መንግሥቱ ተክሌን ጨምሮ አጠቃላይ የትምህርት አመራሮች፣ መምህራንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈውበታል።
‎
‎ዘጋቢ:- እስራኤል ብርሃኑ- ከይርጋጨፌ ጣቢያችን