በጎፋ ዞን በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ሙሉ ወጪ የተገነባው የዱዛ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ህንፃ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሐይማኖቱ መሪዎችና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመረቀ
ዘመናዊና ውብ ገጽታ ያለው ይህ ህንፃ ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ ባሻገር ለአካባቢው ለቱሪዝም መነቃቃት አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተመላክቷል።
ላለፉት 9 ዓመታት የዱዛ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ህንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ በጋሻው በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት፣ እስካሁን የስጦታ፣ የጉልበትና የማሽነሪ ድጋፎችን ሳይጨምር ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አብራርተዋል።
የሳውላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶክተር ማርቆስ ማኖቴ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የተገነባው ቤተ ክርስቲያን ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ ባሻገር መጪው ትውልድ የሚኮራበት ታሪካዊ ቅርስ በመሆኑ ህንፃው ከቱሪዝም መስህብነት አኳያም ለአካባቢው ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አመላክተዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ፣ የጎፋ ህዝብ በሀገር ግንባታና በሀገር መከላከል ታሪክ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ አሻራ አንስተዋል።
ለዚህም አብነት በአድዋ ጦርነት የጎፋ ህዝብ በፈጸመው ጀብዱ ምክንያት በአዲስ አበባ የጎፋ ሰፈር የሚል ስያሜ የተሰጠው አካባቢ መኖሩን ጠቅሰው በዱዛ ተራራ ላይ ይህንን ግዙፍና ውብ ህንፃ የመገንባት ምኞት የቀደሙት አባቶች ቢኖራቸውም፣ ይህ ትውልድ በጋራ በመቆምና በትብብር ምኞቱን እውን ማድረጉ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ ባህሩ በበኩላቸው፣ ምዕመኑ በከፍተኛ ጽናት፣ በአንድነትና በትብብር ይህንን ግዙፍ የቤተ ክርስቲያን ህንፃ ገንብቶ ለምረቃ በማብቃቱ የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸዋል።
በግንባታው ሂደት የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት አስተዳዳሪው፣ በዕለቱም ለቤተ ክርስቲያኑ ከዞኑ አስተዳደር የ300 ሺህ ብር ስጦታ አበርክተዋል።
የጋሞና አካባቢው፣ የጎፋና ባስኬቶ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ለህዝበ ምዕመኑ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በምረቃው ላይ ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች ለተገኙ ሊቀ ጳጳሳት ምስጋና አቅርበው፣ የጎፋና ባስኬቶ ህዝብ ለእምነቱ ተገቢውን ዋጋ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በአካባቢው ሀገረ ስብከት ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ያነሱት ሊቀ ጳጳሱ፣ በዕለቱም ከጋሞ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ለዱዛ ቅዱስ ገብርኤል 100 ሺህ ብር ስጦታ መበርከቱን ገልጸዋል።
በጎፋ ዞን በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ክንውኖች፣ ዝማሬ፣ ወረብና ትምህርቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ለቤተ ክርስቲያኑም የተለያዩ ስጦታዎች ተበርክተዋል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
ከተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች በቤተሰብ እና በጎሳ ደረጀ የሚያደርጉት ባህላዊ የምርቃት ስርአት በየአካባቢው እና በሀገር ደረጀ አንድነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን በማስፈን የመንግስትን የሰላም ግንባታ ግብ ከስኬት ለማድረስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የሀዲያ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ገለጸ።
በዳውሮ ዞን ከ1 መቶ 28 ሺ በላይ ህፃናት በተቀናጀ ሀገር አቀፍ የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ
የቪክቶር ዮኬሬሽ አስደናቂ የብሔራዊ ቡድን ግስጋሴ ቀጥሏል